ከሰባት አመት በፊት በሀገሪቱ ትልቁ ከሆነው ከዚህ እስር ቤት 4000 እስረኞች ማምለጣቸው ይታወሳል
ከእስር ለማምለጥ የሞከሩ 129 ሰዎችን መግደሉን የዲአር ኮንጎ መንግስት አስታወቀ።
የዲሞክራሲያዊ ረፐብሊክ ኮንጎ(ዲአርሲ) መንግስት በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ከሚገኘው ማካላ እስር ቤት ለማምለጥ የሞከሩ ቢያንስ 129 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸሏል።
የሀገሪቱ መንግስት ሁኔታው አሁን ላይ በቁጥጥር ስር ውሏል ብሏል።
የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ሻባኒ ሉኮ በኤክስ ገጻቸው ላይ በዛሬው እለት ባወጡት መግለጫ በአስተዳደር ህንጻው፣ በምግብ ማከማቻው እና በሆስፒታሉ ውስጥ እሳት ተነስቷል። ቢያንስ 59 ሰዎች መቁሰላቸውን ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ባስተላለፉት የቪዲዮ መግለጫ "ከማላካ እስር ቤት በጅምላ ለማምለጥ የተደረገው ሙከራ የሰው ህይወት እንዲጠፉ እና ንብረት እንዲወድም ምክንያት ሆኗል" ብለዋል።
ቀደም ሲል የእስር ቤቱ ባለስልጣን ከእስር ቤት የማምለጥ ሙከራው መክሸፉን እና ለማምለጥ የሞከሩት መገደላቸውን ተናግረዋል። የማምለጥ ሙከራው የተደረገው ባለፈው እሁድ እለት ጠዋት ነው ተብሏል።
ከሰባት አመት በፊት በሀገሪቱ ትልቁ ከሆነው ከዚህ እስር ቤት 4000 እስረኞች ማምለጣቸው ይታወሳል።
የእስር ቤቱ የመያዝ አቅሙ 1500 እስረኞችን ቢሆንም 14000 እስረኞች በተጨናነቀ ሁኔታ ታሰረው እንደሚገኙም ተዘግቧል።