ዲአር ኮንጎ ከውጊያ ቀጠና ሸሽተዋል ያለቻቸውን 25 ወታደሮች በሞት እንዲቀጡ ወሰነች
የተመደቡበትን ስትራቴጂካዊ ስፍራ ለጠላት ለቀው ወጥተዋል የተባሉት ወታደሮች መደብር ሲዘርፉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውም ተገልጿል
የሀገሪቱ ጦር ኤም23 ከተባለው ታጣቂ ቡድን ጋር ከፍተኛ ውግያ እያካሄደ ይገኛል
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከውጊያ ቀጠና ሸሽተዋል የተባሉ 25 ወታደሮች ላይ የሞት ቅጣት ውሳኔ አሳለፍች፡፡
የሀገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ወታደሮቹ የተመደቡበትን ስትራቴጂካዊ ስፍራ ለጠላት ሀይል ለቆ ከመሸሽ በተጨማሪ በአካባቢው በነበሩ መደብሮች ላይ ዝርፍያ ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል ብሏል፡፡
ባሳለፍነው ማክሰኞ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት 27 ወታደሮች ከዚህ ቀደምም አሊምቦንጎ በተባለ ስፍራ ለሚገኙ ሚስቶቻቸው ከመደብሮች የሚሰርቋቸውን ቁሳቁሶች ይወስዱ እንደነበር ተደርሶበታል ነው የተባለው፡፡
ውሳኔውን በዛሬው እለት ያሳለፈው ወታደራዊ ፍርድ ቤት በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል 25ቱን በሞት አንድኛውን ወታደር በ10 አመት ጽኑ እስራት ሲቀጣ የወታደሮቹን ሚስቶች እና ሌላ አንድ ወታደር በነጻ አሰናብቷል፡፡
ላለፉት ሁለት አመታት በሩዋንዳ ይደገፋል ከሚባለው ኤም23 ከተሰኘው አማጺ ቡድን ጋር በመዋጋት ላይ የሚገኘው የሀገሪቱ ጦር ባሳለፍነው ግንቦት ወር በተመሳሳይ ክስ 8 ወታደሮቹ ላይ የሞት ቅጣት መወሰኑ ይታወሳል፡፡
አማጺያኑ በሀገሪቱ ምስራቅ ክፍል ወደ ምትገኘው ጎማ የተሰኘች ትልቅ ከተማ እየተጠጉ ነው መባሉን ተከትሎ በመከላከያው ላይ ሪፎርም አድርጊያለሁ ያለችው ሀገሪቱ 223ኛ ሻለቃን ወደ ስፍራው አሰማርታ ነበር፡፡
የሻለቃው ዋና አዛዥ በተጭበረበረ የህክምና ማስረጃ የውጊያውን ስፍራ ትቶ ወደ ከተማ በመመለሱ በስፍራው የተሰማራው ጦር በስፋት በመክዳት እና በመበታተን ላይ ይገኛል፡፡
ከሁለት አመታት በላይ በውግያ ላይ የሚገኝው የሀገሪቱ ጦር በሎጂስቲክ አቅርቦት እጥረት ፣ በውስጥ ክፍፍል እና በውግያ አቅም መዳከም እየተናጠ ይገኛል፡፡
ውግያው ተፋፍሞ በቀጠለበት ሰሜናዊ ኪቩ 2.7 ሚሊየን ሰዎች ሲፈናቀሉ በአጠቃላይ በአማጺው እና በሀገሪቱ ጦር መካከል በተለያዩ ስፍራዎች በሚደረገው ጦርነት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 7.2 ሚሊየን ተሻግሯል፡፡
የኮንጎ ቱትሲዎች እንደሆኑ የሚነገርላቸው የኤም 23 ታጣቂዎች በሩዋንዳ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የሀገሪቱ መንግስት ይከሳል፡፡
የዲአር ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፍሊክስ ቴሽኬዲ የሩዋንዳ መንግስት ለአማጺያኑ የሚያደርገውን ድጋፍ የማያቆም ከሆነ በሩዋንዳ ላይ ጦርነት እናውጃለን ሲሉ ዝተዋል፡፡
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ በበኩላቸው የሚቀርብባቸው ክስ መሰረተ ቢስ ነው በሚል በተደጋጋሚ ሲያጣጥሉ ይደመጣሉ፡፡