4 ሺህ የሩዋንዳ ወታደሮች የኮንጎን መንግስት ለመጣል ከሚታገለው አማጺ ቡድን ጋር ተሰልፈው እየተዋጉ ነው ተባለ
በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል በርካታ ስፍራዎችን እየተቆጣጠረ የሚገኝው የኤም 23 ቡድን በሩዋንዳ ጦር እንደሚደገፍ ተመድ አጋልጧል
በኮንጎ 120 የሚጠጉ ታጣቂ ቡድኖች በተለያየ ምክንያት ከመንግስት ጋር እየተዋጉ ይገኛሉ
የዲአር ኮንጎን መንግሰት ለመጣል ከሚንቀሳቀሰው ኤም 23 አማጺ ቡድን ጋር ተሰልፈው ከ3 እስከ 4ሺ የሚጠጉ የሩዋንዳ ወታደሮች እየተዋጉ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት አጋለጠ፡፡
የሩዋንዳ መንግሰት በአሜሪካ እና በአለም አቀፍ ተቋማት በጦርነቱ ዙርያ ባለው ተሳትፎ የሚቀርብበትን ክስ ሲያስተባብል ቆይቷል፡፡
ከሰሞኑ ተመድ ባወጣው 293 ገጽ በሚደርሰው ሪፖርት የሩዋንዳ ሰራዊት በጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳለው አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ከሀገሪቱ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ክፍለ ጦር የተውጣጡ ናቸው የተባሉት የሩዋንዳ ወታደሮች አማጺ ቡድኑ በሰሜናዊ ኪቩ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ስትራቴጂካዊ ስፍራዎችን እንዲቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው ነው ያለው፡፡
ሩዋንዳ የኮንጎን ሉአላዊነት ተላልፋለች ያለው ድርጅቱ ግጭቱ ከዚህ የበለጠ ከመስፋፋቱ በፊት ሀገሪቱ ጦሯን እንድታስወጣ ጠይቋል፡፡
የኮንጎ ምስራቅ ክፍል ላለፉት ሁለት አመታት ነፍጥ ባነገቡ ታጣቂዎች እየታመሰ ሲሆን በአካባቢው 120 የሚጠጉ ታጣቂዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከፍሊክስ ቴሽኬዲ መንግስት ጋር እየተዋጉ ይገኛሉ፡፡
ምስራቅ ኮንጎ ታጣቂዎች የማአድን ስፍራዎችን ለመቆጣጠር ፣ አካባቢያቸውን ከመንግስት እና ከታጣቂ ሀይሎች ጥቃት ለመከላከል እንዲሁም ፖለቲካዊ አላማ አንግበው የሚዋጉ ታጣቂዎች የሚገኙበት ስፍራ ነው፡፡
በመንግስታቱ ድርጅት ማዕቀብ የተጣለበት ኤም 23 ከሩዋንዳ መንግስት በሚያገኛቸው ዘመናዊ የጦር መሳርያዎች በጦርነቱ በርካታ ስፍራዎችን እየተቆጣጠረ መቀጠሉ በሪፖርቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን ፤ የመካከለኛ ርቀት የአየር መቃወሚያ ፣ ሞርታር እና ሌሎች ከባድ መሳርያዎችን በጦርነቱ ጥቅም ላይ እያዋለ ይገኛል ብሏል፡፡
ከሩዋንዳ ቱትሲ ብሔረሰብ ጋር የደም ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው የኤም 23 አማጺ ቡድኖች የምስራቅ ኮንጎ ትልቋ ከተማ የሆነችውን ጎማ ከተማን መቆጣጠር ችለው ነበር፡፡
ከሁለት አመታት በላይ በውግያ ላይ የሚገኝው የሀገሪቱ ጦር በሎጂስቲክ አቅርቦት እጥረት ፣ በውስጥ ክፍፍል እና በውግያ አቅም መዳከም እየተናጠ ይገኛል፡፡
ውግያው ተፋፍሞ በቀጠለበት ሰሜናዊ ኪቩ 2.7 ሚሊየን ሰዎች ሲፈናቀሉ በአጠቃላይ በአማጺያን እና በሀገሪቱ ጦር መካከል በተለያዩ ስፍራዎች በሚደረገው ጦርነት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 7.2 ሚሊየን ተሻግሯል፡፡
የዲአር ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፍሊክስ ቴሽኬዲ የሩዋንዳ መንግስት ለአማጺያኑ የሚያደርገውን ድጋፍ የማያቆም ከሆነ በሩዋንዳ ላይ ጦርነት እናውጃለን ሲሉ ዝተዋል፡፡
ተመድ በሪፖርቱ መጨረሻ ላይ በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የሚገኝው ሁኔታ እጅግ አስከፊ ነው ያለ ሲሆን በተለይ ውግያ በተፋፋመባቸው አካባቢዎች ያሉት የሰበአዊ ሁኔታዎች አስቸኳይ ምላሽ የሚሹ ናቸው ብሏል፡፡