አፕልን ጨምሮ የዓለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች በኮንጎ አለመረጋጋቶችን ለምን ይደግፋሉ?
የተትረፈረፈ ማዕድን ባለቤት የሆነችው ኮንጎ ከጠቅላላ ህዝቧ ውስጥ 75 በመቶው በቀን ከ2 ዶላር በታች ገቢ የሚያገኝ ነው
በዲሞክራቲክ ኮንጎ ከ250 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት አማጺያን ይንቀሳቀሳሉ
አፕልን ጨምሮ የዓለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች በኮንጎ አለመረጋጋቶችን ይደግፋሉ ተባለ፡፡
ማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ዲሞክራቲክ ኮንጎ የተትረፈረፈ ማዕድናት ያሏት ብትሆንም ህዝቧ ግን አሁንም በድህነት እንደሚኖሩ የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል፡፡
ነፍጥ አንስተው የሚታገሉ በርካታ አማጺ ቡድኖች ያሉባት ዲሞክራቲክ ኮንጎ 240 የሀገር ውስጥ እንዲሁም 14 የውጭ ሀገራት አማጺ ቡድኖች እንዳሉም ተገልጿል፡፡
ሀገሪቱ በተለይም ለኤሌክትሮኒክስ እና ተሽከርካሪ ምርቶች ዋና ግብዓት የሆነው ኮባልት እና ሊቲየም ማዕድናት በስፋት ያለባት ሀገርም ናት፡፡
እንደ አፕል፣ ማይክሮሶፍት እና መሰል የዓለማችን የንግድ ድርጅቶች ከዲሞክራቲክ ኮንጎ የሚመረቱ ማዕድናትን በርካሽ እየገዙ በዓመት በቢሊዮን ዶላር ትርፍ በማግኘት ላይ ናቸው፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች በዲሞክራቲክ ኮንጎ መረጋጋት እንዳይኖር አማጺ ቡድኖችን ይረዳሉ የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን በተለይም በአማጺ ቡድኖች የሚወጡ ማዕድናትን እየገዙ ናቸውም ተብሏል፡፡
የዲሞክራቲክ ኮንጎ መንግስት ጎረቤቷ ሩዋንዳ አማጺ ቡድኖች የሚዘርፉትን ማዕድናት ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ፣ እንዲጓጓዙ እና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገች እንደሆነ በተደጋጋሚ አስታውቃለች፡፡
የሩዋንዳ መንግስት በዲሞክራቲክ ኮንጎ የቀረበባትን ክስ በተደጋጋሚ ውድቅ ያደረገች ቢሆንም በተለይ ኤም23 የተሰኘው አማጺ ቡድን ጎማ ከተማን እና ሌሎች የማዕድን ሀብት ያለባቸው ስፍራዎችን እንዲቆጣጠር ድጋፍ እያደረገች ነው የሚል ክስ ቀርቦባታል፡፡
የዲሞክራቲክ መንግስት እንደ ኮባልት እና ሊቲየም አይነት ማዕድናትን የሚገዙ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በዓመት በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ትርፍ እያገኙ ለድሃ የሀገሪቱ ዜጎች ግን እንደ ትምህርት እና ጤና ጣቢያዎችን አይነት መገልገያ ተቋማትን ሊገነቡ ይገባል የሚል ጥያቄ እየቀረበባቸው ይገኛል፡፡
አሜሪካ፣ ሩዋንዳ የኮንጎ አማጽያንን ትረዳለች መባሉ እጅግ እንዳሳሰባት ገለጸች
ከዚህ በተጨማሪም ተቋማቱ በዲሞክራቲክ ኮንጎ አለመረጋጋት አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸው ላይ ክስ ለመመስረት ሲሞከር እንደ አሜሪካ ያሉ ምዕራባዊን ሀገራት ተቋማቱ በህግ እንዳይጠየቁ የህግ ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በዲሞክራቲክ ኮንጎ ካሉ ጠቅላላ ህዝቦች መካከል 75 በመቶ ያህሉ በድህነት ውስጥ የሚኖር እና ዕለታዊ ገቢቸውም ከ2 ዶላር በታች ነው ተብሏል፡፡
በሀገሪቱ በቅርቡ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተደረገ ሲሆን በዚህ ድርጊት ውስጥ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ተሳትፈዋል መባሉ ይታወሳል፡፡