ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በኬንያ የሚካሄደውን ምርጫ የሚታዘብ የኢጋድ ልዑክን እንዲመሩ ተመደቡ
የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ “እርሳቸው የኢጋድን ልዑክ እንዲመሩ በመመደባቸው ክብር ይሰማናል” ብለዋል
እንደ ኢጋድ ሁሉ አፍሪካ ህብረት ስምንት አባላት ያካተተ ታዘቢ ልዑክ ወደ ኬንያ መላኩ አይዘነጋም
የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ አንደፈረንጆቹ ነሃሴ 9 ቀን 2022 የሚካሄደውን የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚታዘበውን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት (ኢጋድ) ልዑክ እንዲመሩ መመደባቸውን ኢጋድ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።
የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጉዳዩን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፤ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እጅግ የተከበሩ የፖለቲካ መሪ እና ልምድ ያላቸው ዲፕሎማት መሆናቸውን ገልጸው፤ “እርሳቸው የኢጋድን ልዑክ እንዲመሩ በመመደባቸው ክብር ይሰማናል” ብለዋል።
“ኢጋድ የኬንያን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲታዘብ የኬንያ የምርጫ እና የድንበር ጉዳዮች ኮሚሽን እምነት የጣለብን በመሆኑም ክብር ተሰምቶናል” ሲሉም አክለዋል ዋና ጸሃፊው።
ምርጫው ለኬንያውያን ዲሞክራሲያዊ ሰላማዊ እና የተሳካ እንዲሆንም የኢጋድ ዋና ጸሃፊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ምኞታውን ገልፀዋል።
እንደ ኢጋድ ሁሉ የአፍሪካ ህብረትም በአባል ሀገራቱ አማካኝነት የሚካሄዱ ምርጫዎችን የሚታዘብ ሲሆን የዘንድሮውን የኬንያ ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ ስምንት ቡድን ያለው የምርጫ ታዛቢ ልዑክ መላኩን በቅረቡ በድህረ-ገጹ ማስታወቁ አይነጋም፡፡
የምርጫ ታዛቢ ልዑኩ ከምርጫ ቅድመ ዝግጅት እስከ ድህረ ምርጫ ወቅቶች ድረስ ያሉ ስራዎችን በመታዘብ ሪፖርት እንዲያቀርብ ተልዕኮ ተሰጥቶታል ተብሏል፡፡
ኬንያውያን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚመመሩዋቸው መሪ ለመምረጥ ጥቂት ገዚያት ቀርተዋቸዋል፡፡