ራይላ ኬንያን በፕሬዝዳነትንት ለመምራት 5 ጊዜ በእጩነት ቢቀርቡም እስካሁን አልተሳካለቸውም
የ77 ዓመቱ ራይላ ኦዲንጋ የፊታችን ነሀሴ በሚካሄደው የኬንያ ፕሬዝዳናታዊ ምርጫ ላይ ለአምስተኛ ጊዜ እንደሚወዳደሩ አሳውቀው በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ናቸው።
የ77 ዓመቱ ፕሬዝዳንታዊ እጩ በምርጫው አሸንፈው ስልጣን ከያዙ በኬንያ ታሪክ የመጀመሪያዋን ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት እንደሚሾሙ ቃል በመግባት የቀድሞዋን ፍትህ ሚኒስትር ማርታ ካሩዋን መርጠው የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን እንደቀጠሉ ቢቢሲ ዘግቧል።
በኬንያ ባለፉት አራት የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅቶች ላይ እጩ ሆነው ተወዳድረው የተሸነፉት ራይላ ኦዲንጋ ለአራተኛ ጊዜ አሁን በስልጣን ላይ ባሉት ኡሁሮ ኬንያታ ሲሸነፉ ከምርጫ ራሳቸውን እንዳገለሉ ተናግረው ነበር።
ይሁንና ሀሳባቸውን መቀየራቸውን እና ለአምስተኛ ጊዜ ኬንያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት እንደሚወዳደሩ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ኬንያን በምክትል ፕሬዝዳንትነት እየመሩ ያሉት ዊሊያም ሩቶ የራይላ ኦዲንጋ ዋነኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ኬንያን ላለፉት 10 ዓመታት የመሩት እና በሁለት የምርጫ ዘመን ላይ ራይላን አሸንፈው ስልጣን የያዙት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የራይላ ደጋፊ መሆናቸውን አስቀድመው ተናግረዋል።
ራይላ ኦዲንጋ ኬንያ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ከወጣች በኋላ ሀገራቸውን በምክትል ፕሬዝዳንትነት የመሩት ጃራሞጊ ኦዲንጋ ልጅ ናቸው።
ራይላ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት ለችግር ተጋላጭ ኬንያዊያንን ለመደጎም በየወሩ 40 ዶላር በማህበራዊ ፈንድ ስም እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።
እንዲሁም ዕጩ ፕሬዝዳንቱ ሙስና ላይ ሰፊ ስራ እንደሚሰሩ እና ልዩ የጤና ድጋፍ ለዜጎቻቸው እንደሚያደርሱ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ተናግረዋል።
ባለሀብት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ራይላ ኦዲንጋ የአራት ልጆች አባት ሲሆኑ፤ በኬንያ ህዝብ ብዛት በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊዎ የተሰኘው ብሄር ተወላጅ ናቸው።
በኬንያ ንግድ ስራ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ የሖኑት ራይላ ከፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ባለፈ የጋዝ ስሊንደር ማምረቻ ፋብሪካ እና ሌሎች ከነዳጅ እና ጋዝ ንግድ ጋር የተያያዙ ንግዶችን በመስራትም ይታወቃሉ።