ሞርሞ ከድሃው የህንድ ማህበረሰብ የተገኙ መሪ ናቸው
15ኛዋ የህንድ ፕሬዝዳንት በመሆን የተመረጡት ድራኡፓዲ ሙርሞ በዛሬው እለት በኒው ዴሊ በሚገኘው የፓርላማ አዳራሽ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡
በቃለ መሃላ ስነ ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ራጃያ ሳባ ሊቀመንበር እና ምክትል ፕሬዝዳንት ቬንካያህ ናይዱ፣ የሎክ ሳባ አፈ ጉባኤ ኦም ቢራ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት፣ ገዥዎች፣ ዋና ሚኒስትሮች፣ የፓርላማ አባላት እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
ከድሃው የህንድ ማህበረሰብ እንደተወለዱ የሚነገርላቸው ሞርሞ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ "የእኔ መመረጥ በዚህ ሀገር ያሉ ድሆች ህልም እንዲኖራቸና ህልማቸው እውን ማድረግ እንደሚችሉ ማረጋገጫ ነው" ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የሂንዱ ብሄረተኛ ባራቲያ ጃናታ ፓርቲ (ቢጄፒ) ፓርቲ አባል የሆኑት ሞርሞ፤ የህንድ ሁለተኛ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጥ የቻሉ እንስት ናቸው፡፡
ከህንድ 1ነጥብ 3 ቢሊዮን ህዝብ ውስጥ 8 ነጥብ 6 በመቶ ያህሉ ተወላጆች ሲሆኑ የሀገሬው ተወላጆች ብዙውን ጊዜ ድሆች እና የተገለሉ መሆናቸው ይነገራል። እናም ሙርሞ ከተገለለው ማህበረሰብ ወደ መሪነት ስፍራ መምጣታቸው በህንድ ታሪክ ትልቅ እርምጃ ነው ተብሎለታል፡፡
ሙርሙ እንደፈረንጆቹ በ1997 የባህራቲያ ጃናታ ፓርቲ (ቢጄፒ) አባል በመሆን የፖለቲካው ዓለም የተቀላቀሉ ሲሆን፤በአስካሁኑ የፖለቲካ ህይወታቸው የራይራንግፑር ናጋር ፓንቻያት ምክር ቤት አባል፤ በ2000 ፓንቻያት ሊቀመንበር ፣ በኋላም የቢጂፒ ብሔራዊ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መሪ ሆነው ገለገሉ መሪ ናቸው፡፡
በህንድ ፕሬዝዳንት የሚመረጠው በፓርላማ ምክር ቤት አባላት እና በፌዴራል አስተዳደር ስር ባሉ የክልሎች እና የህብረት ግዛቶች ህግ አውጪዎች ነው፡፡