የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት የሀገራቸው ወታደሮች በዲአር ኮንጎ መኖራቸውን እንደማያውቁ ተናገሩ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 4ሺህ የሚደርሱ የሩዋንዳ ወታደሮች ከኤም 23 አማጺያን ጋር ወግነው እንደሚዋጉ ይከሳል
በቅርብ ቀናት በተባባሰው ግጭት ከ900 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል የሩዋንዳ ወታደሮች እንደሚንቀሳቀሱ እንደማያውቁ ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ብዙ የማላውቀው ነገር አለ፤ ጥያቄው በኮንጎ ያለው ግጭት ለሩዋንዳ እንደሚያሰጋት እና ይህን ለመከላከል ምን ታደርጋለች የሚል ከሆነ ደህንነቷን ለማስጠበቅ የትኛውንም ነገር ልታደርግ እንደምትችል ላረጋግጥ እወዳለሁ” ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቱ የሀገራቸው ጠቅላይ ወታደራዊ አዛዥ ቢሆንም በመከላከያ ሰራዊታቸው እንቅስቃሴ ዙሪያ የማውቀው ነገር የለም ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
የኤም 23 አማጺ ቡድን ቃል አቀባይ ቪክቶር ቴሶንጎ ከሩዋንዳ ምንም አይነት ድጋፍ እንደማይደረግላቸው ገልጸው “ይህ ወሬ የሚነዛው ተቀባይነታችንን ለማሳጣት ነው” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ፓትሪክ ሙያ በበኩላቸው “የፕሬዝዳንቱ ንግግር ፍጹም ከእውነታው ጋር የሚጋጭ ነው፤ የሩዋንዳን ወታደራዊ ድጋፍ የሚያረጋግጥ በሰነድ የተደገፈ ማስረጃ አለን” ብለዋል፡፡
በቅርብ ቀናት ውስጥ በኤም 23 አማፂ ቡድን እና በኮንጎ ወታደሮች መካከል እየተባባሰ የሚገኘውን ግጭት ተከትሎ ከ900 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ባሳለፍነው ሳምንት በምስራቃዊ ኮንጎ ጎማ ከተማን የተቆጣጠሩት የኤም 23 አማጽያን በሩዋንዳ እንደሚደገፉ ይከሳሉ፡፡
ተመድ በቀጠናው ከ3 እስከ 4 ሺህ የሚደርሱ የሩዋንዳ ወታደሮች አመጽያኑን በዘመቻ እና በተለያዩ ወታደራዊ ድጋፎች ላይ እገዛ እንደሚያደርጉ ሪፖርት አውጥቷል፡፡
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ በተለያዩ ሰዎች ዘንድ የምስራቅ አፍሪካ ቭላድሚር ፑቲን በሚል ይጠራሉ ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡
ፕሬዝዳንቱ በምላሻቸው “ሰዎች ስለ እኔ ምንም ሊናገሩ ይችላሉ፤ ይህን ልቆጣጠር አልችልም፤ ዋናው የኔ ስራ በሀገራችን ዙሪያ ከሚነፍስ ማንኛውም አውሎ ነፋስ መትረፋችንን ማረጋገጥ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሩዋንዳ በተለያዩ ማዕድናት በበለጸገው ምስራቃዊ ኮንጎ የሚንቀሳቀሱ አማጺያንን በማስታጠቅ እና በመደገፍ ማዕድናቱን ወደ ኪጋሊ ለማዘዋወር ጥረት እያደረገች ነው በሚል ትከሰሳለች፡፡