ተመድ የብሪታኒያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመመለስ እቅድ “ሙሉ በሙሉ ስህተትነው” አለ
ነገ በመጀመሪያው በረራ 37 ስደተኞች ይሳፈራሉ ተብሎ ቢጠበቅም የተገኙት ስደተኞች 10 አይሞሉም ተብሏል
የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ብሪታኒያ “ህገ ወጥ ስራ እየሰራች ነው” ብለዋል
የብሪታኒያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመመለስ እቅድ “ሙሉ በሙሉ ስህተት” ነው ሲሉ የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ ተናገሩ።
ኮሚሽነሩ ብሪታኒያ “ህገ ወጥ ስራ እየሰራች ነው” ማለታቸውን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል /ኤኤፍፒ/ ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ የሚያደርጉት የመጀመሪያው ዙር በረራ በነገው እለት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።
በነገው ማክሰኞ እለት በሚኖረው በረራ 37 ስደተኞች ይሳፈራሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበረ ቢሆኑም፤ አስካሁን ባለው መረጃ ወደ ሩዋንዳ ያቀናሉ ከተባሉት ስደተኞች አስር እንኳን አለመገኘታቸው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።
አውሮፕላኗ ከመነሳቷ በፊት ምናልባትም ሁሉም ተሳፋሪዎች እንዳያመልጡ የሚል ስጋት እንዳለም ተገልጿል።
ሩዋንዳ፤ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ስደተኞችን ለማስተናገድ የሚያስችል የሚልየን ዶላሮች ስምምነት ባለፈው ወር ከብሪታኒያ ጋር መፈራረሟ የሚታወስ ነው።
በስምምነቱ መሰረት፤ ብሪታኒያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመመለሱ ተግባር በፈረንጆቹ ሰኔ 14 ቀን 2022 ጀምሮ ማከናወን እንደምትጀምር ማስታወቋም አይዘነጋም።
ይህ አከራካሪ ሆኖ እየቀጠለ የመጣው ጉዳይ “የፈጣሪን ስራ የሚጻረር” ተግባር መሆኑ ከሃይማኖት መሪዎች ጀምሮ እስከ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲተቹት የነበረ ጉዳይ መሆኑም የሚታወቅ ነው።
በመጠለያዎች ውስጥ ከነበሩ ስደተኞች ጥቂት የማይባሉ እየጠፉ እንደሆነም ሲነገር ቆይቷል።
ይሁን እንጂ አወዛጋቢው የጥገኝት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ የመመለስ ጉዳይ፤ በመጨረሻም ቢሆን በብሪታኒያ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ከቀናት በፊት ይሁኝታ ማግኘቱ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ “በደስታ የተቀበልኩት ዜና” ማለታቸውም እንዲሁ ይታወቃል።
ጉዳዩን አጥብቀው ሲቃወሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ሲያደርጉት ነበረ ጥረት ባይሳካላቸውም፤ “በግዳጅ ሊባረሩ” የተዘጋጁት ሰዎች ደኅንነት እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።
ብሪታኒያ በርካታ ስደተኞች ከሚያስተናግዱ ሀገራት አንዷ መሆኗ ስትሆን፤ በዚህ ዓመት ብቻ ከ4 ሺህ 850 በላይ ስደተኞች ወደ ብሪታኒያ ገብተዋል፤ ቁጥሩ ባለፈው ዓመት ከነበረው 831 የስደተኞች ቁጥር በእጅጉ የላቀ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ወደ ስልጣን ሲመጡ የህገ ወጥ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ቃል ቃል ገብተው እንደነበር የሚታወስ ነው።