ብሪታኒያ፤ በ'ሩዋንዳ አሰፍራቸዋለሁ' ባለቻቸው ስደተኞች ጉዳይ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ጣልቃ እየገባባት እንደሆነ አስታወቀች
የተመድ ስደተኖች ኤጀንሲ የብሪታኒያ እቅድ “ሙሉ በሙሉ ስህተት” ነው ማለቱ ይታወሳል
ፍርድ ቤቱ ማክሰኞ እለት ወደ ሩዋንዳ ሊደረግ የነበረውን የስደተኞች በረራ አግዷል
ብሪታኒያ፤ በ'ሩዋንዳ አሰፍራቸዋለሁ' ባለቻቸው ስደተኞች ጉዳይ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ጣልቃ እየገባባት እንደሆነ አስታወቀች፡፡
ብሪታኒያ ይህን ያለችው፤ ፍርድ ቤቱ ባሳለፍነው ማክሰኞ ለማከናወን ታስቦ የነበረውን ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የማጓጓዝ የመጀመሪያ ዙር በረራ ማገዱን ተከትሎ ነው፡፡
በዚህም የብሪታኒያ መንግስት “ፍርድ ቤቱ በረራውን ማገድ አልነበረበትም” ብሏል፡፡
ማክሰኞ እለት ስደተኞችን በመያዝ ከብሪታኒያ ወደ ሩዋንዳ ለመብረር በዶቨር አውሮፕላን ማረፊያ በዝግጅት ላይ የነበረ ጉዞውን መሰረዙ የሚታወስ ነው፡፡
ጉዞው የተሰረዘው በመጨረሻዎቹ የበረራ ሰአታት በተላለፈ ውሳኔ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
በረራው ሊሰረዝ የቻለውም በስትራዝቦርግ የሚገኘው ህብረቱ ፍርድ ቤት፤ ብሪታኒያ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ከመመለሷ በፊት ከውሳኔው ህጋዊነት ጋር የተያያዙ ምርመራዎች ማድረግ አስፈላጊ ነው በማለቱ ነበር፡፡
የበረራውን መሰረዝ የተቃወሙት የብሪታኒያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ትክክል አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፕሪቲ ፓቴል “ለቀጣይ በረራ ከዛሬ ጀምሮ ዝግጅት መደረጉ ይቀጥላል”ም ነበር በወቅቱ ያሉት፡፡
ሚኒስትሯ እንዲህ ይበሉ እንጂ፤ ይህ አከራካሪ ሆኖ እየቀጠለ የመጣው ጉዳይ “የፈጣሪን ስራ የሚጻረር” ተግባር መሆኑ ከሃይማኖት መሪዎች ጀምሮ እስከ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲተቹት የነበረ ጉዳይ መሆኑም የሚታወቅ ነው።
በመጠለያዎች ውስጥ ከነበሩ ስደተኞች ጥቂት የማይባሉ እየጠፉ እንደሆነም ሲነገር ቆይቷል።
የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ፤ የብሪታኒያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሩዋንዳ የማስፈር እቅድ “ሙሉ በሙሉ ስህተት” ነው ሲሉ መቃወማቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ብሪታኒያ “ህገ ወጥ ስራ እየሰራች ነው” ም ነበር ያሉት ኮሚሽነሩ፡፡
ብሪታኒያ በርካታ ስደተኞች ከሚያስተናግዱ ሀገራት አንዷ ነች፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ከ4 ሺህ 850 በላይ ስደተኞች ወደ ብሪታኒያ ገብተዋል፡፡ ቁጥሩ ከባለፈው ዓመት የስደተኞች ቁጥር በ831 የጨመረ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ወደ ስልጣን ሲመጡ የህገ ወጥ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ቃል ገብተው እንደነበር የሚታወስ ነው።