ኢራን የጸጥታው ም/ቤት ውሳኔን በመጣስ ለኢትዮጵያ ድሮን መሸጣን አሜሪካ አስታወቀች
ኢራን ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን (ድሮን) ለኢትዮጵያ የሸጠችው ከአንድ ዓመት በፊት ነው ተብሏል
ኢራን “ሞሃጀር” የተሰኘውን ድሮን ለኢትዮጵያ መስጠቷን አሜሪካ ገልጻለች
ኢራን የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔን በመጣስ ለኢትዮጵያ ድሮን መሸጧን አሜሪካ አስታወቀች።
የአሜሪካ መንግስት እንዳሳወቀው ኢራን ከአንድ ዓመት በፊት ክረምት ላይ ለኢትዮጵያ ሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮን ማስተላለፏን ገልጿል።
ኢራን በፈረንጆቹ 2015 ላይ የጦር መሳሪያ ግብይት እንዳትፈጽም የሚከለክል ማዕቀብ በመንግስታቱ ድርጅት የተወሰነባት ሲሆን፤ ይሄንን ማዕቀብ በመጣስ ለኢትዮጵያ አስተላልፋለች ተብሏል።
2231 የተሰኘው ይህ የተመድ ውሳኔ በኢራን መጣሱን የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቪዳንት ፓቴል መናገራቸውን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ በ2020 ላይ የሚያበቃ ቢሆንም በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ማዕቀቡ እንዲራዘም ጠይቀው ነበር።
ይሁንና ይህ ማዕቀብ እንዲነሳ ያልተወሰነ በመሆኑ ኢራን ውሳኔውን በመጣስ ለኢትዮጵያ አሳልፋ ሰጥታለች ተብሏል፡።
እንደዘገባው ከሆነ ኢትዮጵያ ከኢራን የተረከበችውን ሞሃጀር የተሰኘውን ይሄንን ድሮን ከህወሃት ጋር በሚደረገው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ እንዳዋለችውም ተገልጿል።
ኢራን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የጦር መሳሪያ ማዕቀቡን በመተላለፍ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ለጀመረችው ጦርነት ድሮን ለሞስኮ ማስተላለፏንም አሜሪካ አስታውቃለች።
ኢራን በምዕራባዊያን የሚቀርቡባትን ክሶች ውድቅ ያደረገች ቢሆንም ከሩሲያ ጋር የሰው አልባ አውሮፕላን እና ሚሳኤል ግዢ ስምምነት መፈጸሟን አምናለች።
ዩክሬን በበኩሏ ኢራን ሻሂድ፣ጄራን እና ሌሎች ስያሜ ያላቸውን ድሮኖች ለሩሲያ በመሸጥ የዩክሬን ዋና ዋና ከተሞች እንዲደበደቡ አድርገዋል በሚል ከቴህራን ጋር ያላትን ግንኙነት እንደምታቋርጥ ዝታለች።