የሰሜን ኮሪያ ድሮን ሴኡል በሚገኘው የፕሬዝዳንት ቢሮ አቅራቢያ ታየች
ደቡብ ኮሪያ ለበረራ በተከለከለው ቀጠና የፒዮንግያንግ ድሮን ለአጭር ጊዜ መብረሯን አምናለች
ሴኡል ማንኛውንም የሰሜን ኮሪያ ጥቃት ለመጋፈጥ ያላት ዝግጁነት ጥያቄ ተነስቶበታል
የሰሜን ኮሪያ ድሮን በደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡል ፕሬዚዳንታዊ ጽሕፈት ቤት አቅራቢያ ለበረራ የተከለከለ ቀጠናን ጥሳ ማለፏ ተገለጸ።
የፒዮንግያንግ ድሮን ለበረራ በተከለከለው ቀጠና ሰሜናዊ ክፍል ነው ማለፏ የተነገረው።
ደቡብ ኮሪያ ቀደም ሲል መረጃውን ብታስተባብልም የሀገሪቱ ወታደራዊ ባለስልጣን ለዮንሃፕ የዜና አገልግሎት በሰጡት ማብራሪያ ድሮኗ ለአጭር ጊዜ የተከለከለውን ቀጠና ጥሳ ማለፏን አረጋግጠዋል።
ይሁን እንጂ ወደዋናው የደህንነት ቢሮ አለቀረበችም ብለዋል ስማቸው ያልተጠቀሰው የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣን።
ከበረራ የተከለከለው ቀጠና 3 ነጥብ 7 ኪሎሜትርን የሚሸፍን ሲሆን ፥ የደህንነት ተቋሙ ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት በ4 ኪሎሜትር ላይ ይገኛልም ተብሏል።
የሰሜን ኮሪያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ጎረቤቶቹ ሀገራትን የሚለያየው ወታደራዊ ድንበርን ጥሰው ሲገቡ የትናንቱ ለአምስተኛ ጊዜ ነው ተብሏል።
በፈረንጆቹ ታህሳስ 26 2022 አምስት የሰሜን ኮሪያ ድሮኖች ሴኡልን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች የአምስት ስአት ቆይታ አድርገው ወደመጡበት መመለሳቸው የሚታወስ ነው።
ይህም የደቡብ ኮሪያን የአየር መቃወሚያ ስርአት ጥያቄ ውስጥ እንደከተተው አይዘነጋም።
ሴኡል “ራሱን የቻለ የድሮን ወታደራዊ ክንፍ አቋቁማለሁ፤ ለዚህም 440 ሚሊየን ዶላር መድቤያለሁ” ባለች ማግስት ግን የፒዮንግያንግ ድሮን በሴኡል ታይታለች።
የፕሬዝዳንት የን ሱክ የል አስተዳደር በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ማብራሪያን አልሰጠም።
ሴኡል የጎረቤቷን የሰሜን ኮሪያ ጥቃት ለመጋፈጥ ያላት ዝግጁነት ግን ደቡብ ኮሪያውያንን እያጠያየቀ ይገኛል።