የኮፕ28 አየር ንብረት ጉባኤ ታሪካዊ እንደሚሆን ጆን ኬሪ ተናገሩ
በዱባይ የሚካሄደው ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ ዓለምን የሚቀይሩ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ይሆናልም ብለዋል
የኮፕ28 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የፊታችን ህዳር በአረብ ኢምሬትስ ይካሄዳል
የኮፕ28 አየር ንብረት ጉባኤ ታሪካዊ እንደሚሆን ጆን ኬሪ ተናገሩ፡፡
የዘንድሮው ዓለም አቀፉ የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አልያም ኮፕ28 የፊታችን ህዳር በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ዱባይ ይካሄዳል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የአየር ንብረት ጉዳዮች አማካሪው ጆን ኬሪ በዚህ ጉባኤ ዙሪያ ከአልዐይን ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ጆን ኬሪ በቆይታቸው ኮፕ28 በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ታሪክ ወሳኝ የሚባሉ ውሳኔዎች የሚተላለፍበት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
- የአል ጀበር የኮፕ 28 ፕሬዝዳንትነት ለአፍሪካ ምን ፋይዳ አለው?
- ኤሚሬትስ በአፍሪካ የታዳሽ ሃይል ፕሮጀክቶችን ለመርዳት “ኢትሃድ 7” የተሰኘ ፕሮግራም ይፋ አደረገች
ከስምንት አመት በፊት በፈረንሳይ አስተናጋጅነት በፓሪስ ከተማ በተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ታሪካዊ ውሳኔ መተላለፉን ያወሱት ጆን ኬሪ፥ በዘንድሮው የኮፕ28 ጉባኤም የፓሪስ ስምምነት ነጥቦች ወደ ተግባር የሚቀየሩበት ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ከኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን ቢን አል ጀበር ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰው፥ የኮፕ28 ፕሬዛዳንት ጉባኤው በስኬት እንዲካሄድ እንደሚያደርጉ ጽኑ እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በኮፕ28 የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በአለማቀፍ ደረጃ በፈረንጆቹ 2030 ላይ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ በካይ ጋዝ መጠንን በ43 በመቶ ለመቀነስ የተቀመጠውን እቅድ ሊያሳኩ የሚችሉ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ይጠበቃልም ነው ያሉት።
ጆን ኬሪ አክለውም በተለይም በኮፕ28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ዓለም ወደ ታዳሽ ሀይል መሸጋገር የምትችልበት የጋራ መግባባት ላይ መድረስን ጨምሮ ወደ ከባቢ አየር በሚለቀቁ በካይ ጋዝ ምክንያት የደረሱ ጉዳቶች እና ካሳን በሚመለከት የትግበራ ስርዓት ይጸድቃሉ ብዬ እጠብቃለሁም ብለዋል፡፡