17ኛው ‘ዱባይ ኤር ሾው 2021’ ትናንት እሁድ በዩኤኢ ተከፍቷል
17ኛው የዱባይ የአውሮፕላን አውደ ርዕይ (‘ዱባይ ኤር ሾው 2021’) ትናንት እሁድ በታላቋ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የንግድ ከተማ ዱባይ ተጀምሯል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መካሄድ ሳይችል የቆየው አውደ ርዕዩ የዓለም ኤሮስፔስ እና አቪዬሽን ዘርፍ አካል የሆኑ በርካታ ተቋማትን አሳትፎ ነው ትናንት እሁድ የተከፈተው፡፡
በአውደ ርዕዩ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የዱባዩ ልዑል ሼክ ሃምዳን ቢን መሃመድ ቢን ረሺድ አል መክቱም ተገኝተዋል፡፡
ከ148 ሃገራት ተውጣጥተው በ20 የመታያ እልፍኞች (ፓቪሊየንስ) የከተሙ 1 ሺ 200 የዘርፉ አንቀሳቃሾች በአውደ ርዕዩ በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
ከ160 የሚልቁ የመንገደኞች፣ ወታደራዊ እና ቦይንግ 777x እንዲሁም ቦምባርዲዬር ግሎባል 7500ን መሰል የግል አውሮፕላኖች በዐውደ ርዕዩ ቀርበው እየተጎበኙ ነው፡፡
በተለያዩ የአየር ላይ ትርዒቶች ደምቆ ቀጣዮቹን 5 ቀናት የሚቆየው አውደ ርዕዩ እስከ መጪው ሃሙስ ህዳር 9 ቀን 2014 ዓ/ም ይዘልቃል፡፡
በዓለም የአቪየሽን ዘርፍ የገዘፈ ስም ያለውን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የኡጋንዳ እና ሌሎችም ስመ ጥር አየር መንገዶች በአውደ ርዕዩ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ የጦር አውሮፕላኖች፣ ጄቶች፣ ሄሊኮፕተሮች የአውደርዕዩ አካል ናቸው፡፡
ለጉዞ፣ ለወታደራዊ እና ለሌሎችም ግልጋሎቶች የሚውሉ አውሮፕላኖችንና ሄሊኮፕተሮችን አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡ ቦይንግን እና ኤርባስን መሰል ግዙፍ የዓለማችን የአቪዬሽን ተቋማትም ምርቶቻቸውን ይዘው በአውደ ርዕዩ ተገኝተዋል፡፡
በአውደ ርዕዩ የተገኙት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ምክትል ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም የዱባይ ገዢ የሆኑት ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ አል መክቱም አውደ ርዕዩ “ካለፉት 2 ፈታኝ አመታት በኋላ እየተነቃቃ የመጣውን የአቪዬሽን ዘርፍ፤ በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ውጤቶች መልክ ለማስያዝ የሚበጅ ጥሩ አጋጣሚን ለመፈጠር የሚያስችል ነው” ብለዋል።
ሃገራቸው ይህን መሰል ግዙፍ ዓለም አቀፍ ሁነት በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጀት በመቻሏ መኩራታቸውንም ነው ሼክ መሃመድ የተናገሩት፡፡
አውደ ርዕዩ የኤሮስፔስ እና አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ የደረሰበት ደረጃ መታያ ስፍራ ሆኖ ከማገልገልም ባለፈ ገዢና ሻጭ የሚገናኙበት የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት ነው፡፡
ሊዚህ ማሳያ የሚሆኑና ከፍተኛ ገንዘብ የወጣባቸው ስምምነቶች እየተደረጉም ነው፡፡
የአውደ ርዕዩ አዘጋጇ ዩኤኢ በጦር ኃይሏ በኩል ቴልስ እና ጉድሪች ከተባሉ የቴክኖሎጂ አምራች ተቋማት ጋር በድምሩ ከ5 ቢሊዮን ዲርሃም የሚበልጥ ዋጋ ያላቸው ስምምነቶችን ፈጽማለች፡፡
አውደ ርዕዩ ገና ሁለተኛ ቀኑ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ሌሎች ስምምነቶች ገና እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡