ዩኤኢ፣ እስራኤል፣ አሜሪካ እና ህንድ የጋራ የምጣኔ ሃብት ፎረምን ሊያቋቁሙ ነው
ዩኤኢ ባሳለፍነው ዓመት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ማድረግ መጀመራቸው ይታወሳል
የሃገራቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባደረጉት የጋራ የበይነ መረብ ውይይት ነው ፎረሙ እንዲቋቋም የተወሰነው
ዩኤኢ፣ እስራኤል፣ አሜሪካ እና ህንድ በምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት እና ለመተባበር የሚያስችል የጋራ ፎረም ሊያቋቁሙ ነው፡፡
ፎረሙ የአሜሪካ፣ የዩኤኢ፣ የእስራኤል እና የህንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባደረጉት የጋራ የበይነ መረብ ውይይት ነው እንዲቋቋም የተወሰነው፡፡
የበይነ መረብ ውይይቱ በአንቶኒዮ ብሊንከን፣ በሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ እና በጄይ ሻንከር መካከል የተካሄደ ነው፡፡
በእስራኤል ጉብኝት ላይ የነበሩት ጄይ ሻንከር እስራኤል ሆነው ነው በበይነ መረብ ውይይቱ የተሳተፉት፡፡
‘ታሪካዊ’ የተባለው የዩኤኢ እና የእስራኤል ስምምነት
በበይነ መረብ ውይይቱ መሳተፋቸውን በማስታወቅ ውይይቱን የተመለከተ መረጃን በይፋዊ የትዊተር የማህበረሰብ ትስስር ገጻቸው ያጋሩት የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዬር ላፒድ “ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት ትብብር ፎረምን ለማቋቋም ወስነናል፤ ስለተለያዩ የጋራ የመሰረተ ልማት ፕሮጄክቶችም ተወያይተናል” ሲሉ አስፍረዋል፡፡
የጋራ መሰረተ ልማቶቹ በትራንስፖርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በማሪታይም እና በሌሎች የንግድ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚችሉም ነው ላፒድ ያስታወቁት፡፡
የዩኤኢ፣ የእስራኤል እና የህንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከሰሞኑ በዋሽንግተን ጉብኝት ላይ ነበሩ፡፡
በጉብኝቱ ከአየር ንብረት እና ሃይማኖታዊ አብሮነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን ሁለት አዳዲስ የሶስትዮሽ የስራ ቡድኖችንም አቋቁመዋል፡፡
የእርስበእርስ ወዳጅነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከርም ነው ሃገራቱ የተስማሙት፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና እስራኤል ባለፈው ዓመት ዲፕሎማሲያዊ ቅራኔዎቻቸውን ፈትተው የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማድረግ መስማማታቸውን ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ እና ሌሎች የትብብር ግንኙነቶችን ማድረግ መጀመራቸው ይታወሳል፡፡