ዱባይ የምታስተዋውቀው የካርበን ክሬዲት የግብይት ስርአት
ካርበን ክሬዲት ከተፈቀደላቸው መጠን በታች ካርበን የሚለቁ ኩባንያዎች ትርፉን የሚሸጡበት ስርአት ነው
አረብ ኤምሬትስ የካርበን ክሬዲት የግብይት ስርአት ከኮፕ28 ጉባኤ ጎን ለጎን ነው የምታስተዋውቀው
አለማቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ28) ሊጀመር ሶስት ቀናት ቀርተውታል።
በዚህ ጉባኤ ከሚጠበቁ አበይት ሁነቶች መካከል የዱባይ የፋይናንስ ገበያ የሚያስተዋውቀው የካርበን ክሬዲት ግብይት ስርአት ነው።
የካርበን ክሬዲት ከተፈቀደላቸው መጠን በታች የሚበክሉ ኩባንያዎች ትርፉን የሚሸጡበት ስርአት ነው።
ከ17 በላይ የኤምሬትስ ኩባንያዎችን ያካተተው የግብይት ስርአት ከታህሳስ 4 እስከ 8 2023 በዱባይ ለተለያዩ አለማቀፍ አልሚዎች ይተዋወቃል ተብሏል።
በሙከራ ደረጃ የሚተዋወቀው የካርበን ክሬዲት የግብይት ስርአት ኤምሬትስ በ2050 ከካርበን ብክለት የጸዳች ለመሆን የያዘችውን እቅድ የሚደግፍ መሆኑም ነው የተገለጸው።
የግብይት ስርአቱ ከተቀመጠላቸው ኮታ በላይ ካርበን ለሚለቁ ኩባንያዎች በክፍያ የካርበን ክሬዲት እንዲገዙ፤ ከኮታቸው በታች በካይ ጋዝ ለሚለቁትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለሚሰሩ ሀገራትና ኩባንያዎች ደግሞ የገበያ እድል ይዞ የሚመጣ ነው።
የካርበን ክሬዲት ምንድን ነው?
የካርበን ክሬዲት ወይም የካርበን ልቀት ድርሻ ሽያጭ ሀገራትና ኩባንያዎች በካይ ጋዝን መቀነስ ካልቻሉ በሚል የቀረበ አማራጭ ነው።
በዋናነት የበለጸጉትና በካይ የሆኑት ሀገራት ካርበን ክሬዲት በመግዛት ካርበን ዳይ ኦክሳይድ እና ሌሎች በካይ ጋዞችን እንዲለቁ የሚፈቅደው አማራጭ በብክለት ለሚጎዱ ሀገራት ሊደረግ የሚገባን ድጋፍም ያስቀምጣል።
የካርበን ክሬዲት ግዙፍ ኩባንያዎች እስከ 1 ቶን ካርበን ዳይ ኦክሳይድ እንዲለቁ ይፈቅዳል፤ ቀስ በቀስ ልቀታቸውን እንዲቀንሱና የሚለቁትን ካርበን ከከባቢ አየር ላይ እንዲያስወግዱም ያሳስባል።
የካርበን ክሬዲት ተጠቃሚዎች በታዳጊ ሀገራት የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ለማገዝ የሚውል መዋዕለ ንዋይ ያፈሱ ዘንድም ይጠየቃሉ።ካርበን ትሬዲንግ ወይም ኢሚሽን ትሬዲንግ የብክለት መጠናቸውን ለሚቀንሱ ኩባንያዎች ማበረታቻ በመስጠት ብክለትን መቆጣጠር የሚያስችል የገበያ ስርአት ነው።
ከተፈቀደላቸው አሎዋንስ ወይም መጠን በታች የሚበክሉ ኩባንያዎች፣ ከተፈቀደላቸው በላይ መልቀቅ ለሚፈልጉ ኩባንያዎች የተረፋቸውን መጠን መሸጥ የሚያስችለው የካርበን ክሬዲት ሽያጭ ኩባንያዎች የሚያደርሱት የብክለት መጠን እንዲቀንሱ ያበረታታል ተብሎ ይታመናል።
የአየር ንብረት ጥበቃ ተሟጋቾች ግን የካርበን ልቀት ድርሻ ሽያጭ ወይም ካርበን ክሬዲት በካይ ጋዞችን በብዛት የሚለቁ ሀገራትና ኩባንያዎች ብክለታቸውን እንዲገፉበት እንደመፍቀድ ይቆጥሩታል።