መንግስታት የካርበን ጋዝ ግብር ፖሊሲ እንዲነድፉ አይኤምኤፍ አሳሰበ
የግል ድርጅቶች ወደ ከባቢ አየር በሚለቁት በካይ ጋዝ መጠን ግብር ሊከፍሉ ይገባል ተባሏል
መንግስታት የካርበን ጋዝ ግብር ካልጣሉ ያልተከፈለ ብድር መጠን ከፍ ሊል እንደሚችል ድርጅቱ አስጠንቅቋል
መንግስታት የካርበን ጋዝ ግብር ፖሊሲ እንዲነድፉ አይኤምኤፍ አሳሰበ።
የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን መፍትሄዎች በአፋጣኝ በሚያስፈልጉበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ዜጎች በከፍተኛ ሙቀት፣ ቅዝቃዜ፣ ጎርፍ እና ድርቅ በየጊዜው እየተሰቃዩ ሲሆን የሰው ልጆች ያልተገደበ የሀይል ፍላጎት ደግሞ ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ዋነኛው ምክንያት ነው።
ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም አይኤምኤፍ እንዳለው የካርበን ጋዝ ግብር መጣል ትክክለኛ መፍትሄ እንደሚሆን አስታውቋል።
በድርጅቱ የፊሲካል ጉዳዮች ዳይሬክተር ቪቶር ጋስፓር እንዳሉት ወደ ከባቢ አየር ለሚለቀቀው በካይ ጋዝ መጠን ልክ ግብር እንዲከፈል ማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከያ ዋናው መንገድ ነው ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም በተቋማት ላይ የካርበን ጋዝ ግብር ቢጣል ሁሉም ወደ ከባቢ አየር ለሚለቀቀው በካይ ጋዝ ሀላፊነት መውሰድ እንደሚጀምር ተናግረዋል።
የካርበን ጋዝ ግብር መንግስታት ከግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ እንዲሰበስብ እና ለአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት እንዲሰጠው ያደርጋልም ተብሏል።
መንግስታት የካርበን ግብርን ተግባራዊ ካላደረጉ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የሚወስዷቸው ብድሮች መጠን ከዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገታቸው እስከ 50 ድርሻ ሊኖረው እንደሚችልም ተገልጿል።
የካርበን ግብር ማስከፈል ከተጀመረ ተቋማት የሀይል ምንጫቸውን በፍጥነት ወደ ታዳሽ ሀይል ወደማዛወር እይሸጋገራሉም ተብሏል።
የካርበን ግብርን ለመጣል እስካሁን 50 ሀገራት የተቀበሉ ሲሆን ተጨማሪ 20 ሀገራት ደግሞ ፖሊሲዎችን እየመረመሩ እንደሆነ ተገልጿል።