6ኛው የአፍሪካ ግሎባል ቢዝነስ ፎረም በመጪው ጥቅምት በዱባይ እንደሚካሄድ ተገለጸ
የአፍሪካ የድህረ ኮሮና ምጣኔ ሃብታዊ የእድገትና ትብብር ጉዳዮች በጥልቀት እንደሚዳሰሱበትም ነው የተገለጸው
ፎረሙ የአፍሪካ የንግድ ተቋማትን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ለማሳደግ ያስችላል ተብሏል
6ኛው የአፍሪካ ግሎባል ቢዝነስ ፎረም በመጪው ጥቅምት በዱባይ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡
ፎረሙ ከ‘ዱባይ ኤክስፖ 2020’ ጎን ለጎን “በንግድ መለወጥ” (Transformation through Trade) በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ አዘጋጁን የዱባይ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤትን ዋቢ አድርጎ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዜና አገልግሎት (ዋም) ዘግቧል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢ ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ አል መክቱም የበላይ ጠባቂነት የሚዘጋጀው ‘ዱባይ ኤክስፖ 2020’ 173 ሃገራትን እና 24 ዓለም አቀፍ ተቋማትን ያሳትፋል፡፡
ምክር ቤቱ በመግለጫው ፎረሙ አፍሪካ ለሚገጥሟት አዳዲስ ተግዳሮቶች የሰጠቻቸው ምላሾች እና ፈጠራ፣ ትብብር እና ንግድ የፈጠሯቸው አስቻይ ሁኔታዎች የሚገመገሙበት ነው ብሏል፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ የተጎዳው የዓለም ምጣኔ ሃብት እንዴት ባሉ መንገዶች ሊያገግም እንደሚችል በሚቃኝበት በዚህ ፎረም የአፍሪካ የድህረ ኮሮና ምጣኔ ሃብታዊ የእድገትና ትብብር ጉዳዮች በጥልቀት ይዳሰሳሉ፡፡
ፎረሙ ዓለም አቀፍ ተደራሽነታቸውን ማስፋት የሚፈልጉ የአፍሪካ የንግድ ተቋማት ዱባይን እንደ መግቢያ በር ለመጠቀም እንዲችሉ ያበረታታል፡፡
በአፍሪካ እና በዱባይ መካከል ያለውን የንግድና የምጣኔ ሃብት ትስስር ለማሳደግ እንደሚያስችልም ነው የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃማድ ቡዓሚን የተናገሩት፡፡
ተቋማቱ ያላቸውን አቅምና ተደራሽነት የሚያሳዩበት ዓለም አቀፍ በንግድ የመተሳሰሪያ መድረክም ነው ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው፡፡
የአፍሪካ ግሎባል ቢዝነስ ፎረም በጎርጎሮሳውያኑ 2013 ነው የተጀመረው፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ከ65 ሃገራት የተውጣጡ የቢዝነስ አንቀሳቃሾችን ጨምሮ 32 የሃገራት መሪዎችን፣ 140 ሚኒስትሮችንና የመንግስት ባለስልጣናትን እንዲሁም 10 ሺ ገደማ ተሳታፊዎችን አስተናግዷል፡፡