“መንግስት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ፖሊሲ እስከ ማሻሻል ደርሷል” - አቶ መላኩ አለበል
መንግስት ለነዳጅ ብቻ በየወሩ እስከ 4.3 ቢሊየን ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ሚኒስትሩ ገልፀዋል
በፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ 1 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ1.17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴና ሩዝ እንዲሁም 60 ሚሊየን ሊትር ዘይት ከውጭ ገብቷል
መንግስት በኢትዮጵያ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ፖሊሲ እስከ ማሻሻል የደረሱ ውሳኔዎችን መወሰኑን የንግድ እና እንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አስታወቁ።
ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚስተዋለው የዋጋ ንረት እና መንግስት የዋጋ ንረቱን ለማስተካካል እየወሰዳቸው ባለው እርምጃ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ መላኩ በማብራሪያቸው፣ ለአንድ ሀገር የኑሮ ውድነት ችግር ወይም ለገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ብዙ ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ፤ በዋናነት ግን ምክንያቱ “በገንዘብ እና በገበያ ላይ በሚኖረው የምርት መጠን የሚኖር አለመመጣጠን ነው” ብለዋል።
ይህም የብርን የመግዛት አቅም ያዳክማል ያሉት ሚኒስትሩ ፣ በመሆኑም “ሰው ባለው ውስን ገንዘብ ኑሮን ለመምራት የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ለመግዛት ይቸገራል፤ ይህም የኑሮ ውድነት እንዲከሰት ያደርጋል” ሲሉም አስታውቀዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመከላከልም ሁለት መፍትሄዎች አሉ ያሉት አቶ መላኩ ፣ ዋናው እና ዘላቂው መፍትሄ ምርትን ማሳደግ እና ወደ ገበያ የሚቀርብ የምርት መጠን እንዲሁም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን መጠን ማሳደግ ነው ብለዋል።
ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ወደ ገበያ የሚገባ እና በገበያ ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን መገደብ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት በዋናነት ከምግብ እና ምግብ ነክ ሸቀጦች ጋር እንደሚገናኝ የሚገልጹት ሚኒስትሩ፣ ይህንን ለማስተካከል የግብርና ምርቶች በስፋት ወደ ገበያ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
በዚህ ረገድ የተሰሩ ስራዎች ውጤት ቢያስመዘግቡም ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያጋጠሙ ያሉ የዋጋ ንረቶች ለኢትዮጵያ ፈተና ሆነው መቀጠላቸውንም አስታውቀዋል።
“ኢትዮጵያ በታሪኳ በረካታ ችግሮችን ያስተናደገችበት ወቅት ቢኖር ይሄ ወቀት ነው፤ ከእነዚህም የሕዳሴ ግድብ የዲፕሎማሲ ፈተናዎች፣ የሰላምና ደህንነትን ችግሮች ፣ ኮቪድ 19፣ የጎርፍ አደጋ እንዲሁም የምርጫው ጉዳይ ከሌሎች የፖለቲካ ሁኔዎች ጋር ተደምረው ስጋቶች እንዲጨምሩ አድርገዋል” ብለዋል ሚኒስትሩ።
ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ በዓለም ድረጃ የምርት አቅርቦት ላይ ችግር መደቀኑን አስታውሰው ፣ እንደማሳያነትም እስከ 700 ዶላር ሲገዛ የነበረው አንድ ቶን ድፍድፍ ነዳጅ አሁን ላይ ከ1000 ዶላር በላይ እየተገዛ መሆኑን አንስተዋል።
ሌሎች ምርቶችም ከኮቪድ 19 በፊት ከነበራቸው ዋጋ እስከ 50 በመቶ እና ከዚያም በላይ የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸውንም አመላክተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዩ የዋጋ ጭማሪዎች ከሀገር ውስጥ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ተዳምረው በኢትዮጵያ የኑሮ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን አቶ መላኩ ተናረዋል።
“የኢትዮጵያ መንግስት ችግሮቹን ለመቋቋም በርካታ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል” ያሉት ሚኒስትሩ ፣ በዚህም በዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ በየወሩ ለነዳጅ ብቻ እስከ 4.3 ቢሊየን ብር ድረስ እያወጣ እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል።
በሀገር ውስጥ ስንዴ በማምረት ከውጭ የሚመጣውን ስንዴ ለማስቀረት በሁሉም ክልሎች ላይ የምርት መጠኑን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
ከዘይት ጋር ተያይዞም ለሀገር ውስጥ የዘይት አምራቾች በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሬ ተፈቅዶ ፣ ጥሬ እቃ አስገብተው ዘይት በስፋት አምርተው እንዲያከፋፍሉ ድጋፍ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉንም ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በተደረገው ማሻሻያ የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ መሰረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ያለውጭ ምንዛሬ ፈቃድ እንዲገቡ (ፍራንኮ ቫሉታ) መፈቀዱን አስታውሰዋል።
ከዚህ ጋር ተያየዞ “አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ450 ሺህ በላይ ኩንታል ስንዴ፣ 720 ሺህ ኩንታል ሩዝ እንዲሁም ወደ 60 ሚሊየን ሊትር ዘይት ከውጭ ገብቷል” ብለዋል።
ይሄ ማለት መንግስት በተዘዋዋሪ መንገድ ዜጎችን እደገፈ ነው አቶ መላኩ እንዳሉት።
የዋጋ ንረት ችግሮችን ከዓለም አቀፍ እና ከሀገራዊ ሁኔታዎች ጋር አያየዞ መመልከት ይገባል፤ ከዋጋ ንረት ችግር መውጫ ቁልፍ ያለው ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ነው በማለትም ዘላቂ መፍትሔውን ጠቁመዋል።