“ኢኮኖሚ በታሰበው ልክ አላሽቆለቆለም”፡ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሁሉም ዘርፎች የማእድን ዘርፍ የተሻለ እድገት አስመዝግቧል ብለዋል
ኢትዮጵያ በ2012ዓ.ም ከእቅዷ 2.9 በመቶ ዝቅ በማለት የ6.1 በመቶ እድገት ማስመዝገቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ
ኢትዮጵያ በ2012ዓ.ም ከእቅዷ 2.9 በመቶ ዝቅ በማለት የ6.1 በመቶ እድገት ማስመዝገቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ
በ2012 ዓ.ም የተመዘገበው የኢትዮጵያ ዕድገት 6.1 በመቶ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይአህመድ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር በተመለከተ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ በሰጡት ወቅት ነው፡፡
በመጀመሪያው ምላሻቸው ኢትዮጵያ 9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ አቅዳ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ 6.1 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን የፕላን ኮሚሽንን ጠቅሰው ገልጸዋል፡፡ ከዕቅዱ አንጻር ምንም እንኳን የ2.9 በመቶ ቅናሽ ቢታይም ዕድገቱ ግን ዓለም ከገጠማት ፈተና አንጻር ትልቅ ዕድገት ነው ብለዋል፡፡
ኮሮና ቫይረስ ከገባ ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ኢኮኖሚውን ዝግ ማድረግ ይገባል የሚሉ ጥያቄዎች ቢኖሩም ጥልቅ ጥናትን ምርምር በማድረግ መምራት በመቻሉ ዕድገት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
የብድር ጊዜ እንዲራዘም ጥያቄዎች መቅረባቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም በሚፈለገው መጠን ባይሆንም ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት አሁን ላይ 3.375 ትሪሊዮን ብር ወይም 107.4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ግብርና ባለፈው ዓመት 4.3 ዕድገት ሲያስመዘግብ፤ ኢንዱስትሪ 9 በመቶ፤ አገልግሎት ዘርፍ 5.3በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ ከሌሎቹ አንጻር ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል የተባለው የማዕድን ዘርፍ 91 በመቶ አድጓል ብለዋል፡፡
በ2012 በጀት ዓመት የባንኮች አጠቃላይ ቅርንጫፎች ብዛት ከነበረበት 5ሺ 341 ወደ 6ሺ 628 ማደጉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የባንኮች የቅርንጫፎች ዕድገት 18 በመቶ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል የባንክ ሂሳብ የነበራቸው ዜጎች 38.7 ሚሊዮን የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸው ዜጎች 50.7 ሚሊዮን መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ በዚህም የገንዘብ አስቀማጮች ዕድገት 31 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ባንኮች አጠቃላይ 1 ትሪሊዮን ብር መሰብሰባቸውንና ለኢንቨስትመንት የሚያበድሩት መጠንም ማደጉን ገልጸዋል፡፡ ከተሰበሰበው ገንዘብ 60 በመቶው በአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ የተሰበሰበ እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኦሮሚያ 13.7 በመቶ ፣በአማራ 7. 3 በመቶ ፤ በደቡብ ደግሞ 5. 2 በመቶ ገንዘብ መሰብሰቡን አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምስረት ላይ ያሉ ባንኮች ጉዳይም በብሔራዊ ባንክ በኩል እየታየ ነው ያሉ ሲሆን እነዚህ ባንኮች ሲመሰረቱ በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡