ዩኤኢ በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ያላትን የንግድ ግንኙነት የሚያጠናክር የ30 ሚሊዬን ዶላር ስምምነት አደረገች
የዩኤኢ እና የአፍሪካ የንግድ ግንኙነት ባለፉት 5 ዓመታት በእጥፍ ፣ ባለፉት 15 ዓመታት ደግሞ በ 8 እጥፍ አድጓል
ስምምነቱ የተደረገው በአቡ ዳቢ የወጪ ንግድ ቢሮ እና በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የንግድ እና ልማት ባንክ መካከል ነው
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) ከምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሃገራት ጋር ያላትን የገቢና ወጪ ንግድ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል የ30 ሚሊዬን ዶላር ስምምነት አደረገች፡፡
ስምምነቱ በአቡዳቢ የወጪ ንግድ ቢሮ (ADEX) እና በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የንግድ እና ልማት ባንክ (TDB) መካከል የተደረገ ሲሆን በዩኤኢ እና በባንኩ አባል ሃገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ያስችላል ተብሏል፡፡
በበይነ መረብ የተደረገውን ስምምነት የፈረሙት የኤዲኤክስ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ሰዒድ አል ጣሂሪ እና የቲዲቢ ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢትዮጵያዊው አቶ አድማሱ ታደሰ ናቸው፡፡
በስምምነቱ መሰረት ኤዲኤክስ ከዩኤኢ የተለያዩ የንግድ እቃዎችን ወደ ተለያዩ የባንኩ አባል ሃገራት ማስገባት ለሚፈልጉ ነጋዴዎች በቲዲቢ በኩል የገንዘብ አቅርቦትና ብድር ያመቻቻል፡፡
ከአቡዳቢ ሚዲያ ኦፊስ እንደተገኘው መረጃ ከሆነ ስምምነቱ የጋራ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥም በላይ የዩኤኢን ኤክስፖርተሮች አቅም ለማጠናከርና ምጣኔ ሃብታዊ ብዝሐነትን ለመፍጠር ያስችላል፡፡
ዩኤኢ ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀ ምጣኔ ሃብትን መገንባት ላይ ትኩረት አድርጋ በመስራት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡
የቲዲቢ ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አድማሱ ታደሰ ፣ የዩኤኢ እና የአፍሪካ የንግድ ግንኙነት ባለፉት 5 ዓመታት በእጥፍ ፣ ባለፉት 15 ዓመታት ደግሞ በ 8 እጥፍ ማደጉን ተናግረዋል፡፡
ይህ እድገት በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን ጠንካራ የንግድ ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት እንደሚያመለክት ጠቅሰው ለፍላጎቱ ስኬት በተደረገው ስምምነት በኩል ለመደገፍ በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከ35 ዓመታት በፊት የተመሰረተው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የንግድ እና ልማት ባንክ ኢትዮጵያን ጨምሮ 22 አባል ሃገራት አሉት፡፡