ዱባይ በልመና የሚተዳደሩ ሰዎችን እያሰረች ነው
በአረብ ኤሚሬትስ ህግ መሰረት የጎዳና ላይ ልመና ክልክል ነው
በልመናን መተዳደርን ለማስቀረት ዘመቻ ላይ ነኝ ያለው የዱባይ ፖሊስ በዘመቻው የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት 178 ሰዎችን አስሬያለሁ ብሏል
የዱባይ ፖሊስ በተለያዩ የከተማዋ ጎዳናዎችና ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች የሚለምኑ ሰዎችን እያሰረ መሆኑን አስታወቀ፡፡
በየዓመቱ የረመዳን ጾም ከመግባቱ አስቀድሞ በልመና የሚተዳደሩ ሰዎችን ሰብስቦ የሚያስረው የከተማዋ ፖሊስ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ባደረጋቸው ዘመቻዎች 178 ሰዎችን ማሰሩን ገልጿል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 134ቱ ወንድ 44ቱ ሴት ናቸው፡፡
እርምጃው ለህዝብ ደህንነትና ወንጀልን ቀድሞ ለመከላክል በሚል የተደረገ መሆኑን የገለጸ ሲሆን በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
ዩኤኢ የሳምንቱን የእረፍት ቀናት ወደ ቅዳሜ እና እሁድ ቀየረች
ለህዝብ ደህንነት ላይ ከባድ ስጋትን ይደቅናሉ ያላቸውን የልመና ተዳዳሪዎችን ህዝብ ከሚበዛባቸው የገበያ ስፍራዎች እንዲሁም መስጊድን ጨምሮ ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አካባቢ እንደሚያድንም ነው የገለጸው፡፡
በአረብ ኤሚሬት የጎዳና ላይ ልመና ክልክል ነው፡፡ ሆኖም ረመዳንን በመሳሰሉ የጾም ወራት የሚለምኑ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል፡፡ ይህ የዜጎችን እዝነት እንደ ድክመት በመቁጠር የሚደረግ ብዝበዛ እንደሆነም ያስቀምጣል፤ ድሆችን መደገፍ የሚፈልጉ ህጋዊ ሰውነትን በተላበሱ የእርዳታ ተቋማት በኩል እንዲደግፉ የመከረው የከተማዋ ፖሊስ፡፡
ህመምን፣ አካል ጉዳትን ወይም ሌሎች የማታለያ መንገዶችን ህጻናትን ጭምር በመጠቀም በየጎዳናው ይለመናልም ነው የሚለው፡፡ ሆኖም ዜጎች አዝነው የሚያደርጉት ምጽዋት ምናልባትም ወንጀልን የበለጠ ሊያበራክት እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪ ለስርቆትና ለተለያዩ ዝርፊያዎች ሊጋለጥ እንደሚችል በመጠቆምም ጉዳዩን በጥብቅ መከታተሉን እንደሚቀጥልም ነው ያስታወቀው፡፡
የተባበሩት አረብ ኢምሬት ከተመሰረተች 50 ዓመት ሞላት
በሃገሪቱ ህግ መሰረት እንደሚያስቀጣ የተነገረለትን ይህን ህግ ተላልፈው በየጎዳናውና በየቤተ እምነቱ ሲለምኑ የሚገኙ ሰዎች እስከ 3 ወር እስራትና እስከ 5 ሺ ዲርሃም የሚደርስ የእስርና የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡
ሰዎችን እያደራጁ ለልመና የሚያሰማሩ ደግሞ በትንሹ 6 ወር እስራትና 10 ሺ ዲርሃም ይቀጣሉ፡፡
ባለፈው ዓመት በልመና ተሰማርተው የነበሩ 458 የእኔ ቢጤዎችን ይዞ እንደነበርም የዱባይ ፖሊስ አስታውቋል፡፡