በዱባይ ኤክስፖ የኢትዮጵያ እልፍኝ በ200 ሺህ ሰዎች መጎብኘቱ ተገለፀ
በኤክስፖው የተሳተፉ 17 ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት አሳይተዋል
3 ሺህ 800 ሰዎች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ፍላጎት አሳይተዋል- የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር
በዱባይ 2020 ኤክስፖ ባለፉት ሁለት ወራት 200 ሺህ ሰዎች ኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶች መጎብኘታቸውን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ስር የኤክስፖ 2020 ዱባይ ኮሚሽን የኤክስፖውን የሁለት ወራት አፈፃፀም ሪፖርት የተመለከተ ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚህ ወቅት ምክትል ኮሚሽነር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ፤ በኤክስፖው ኢትዮጵያ የሰው ዘርና የቡና መገኛ፣ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሁም ምቹ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሉሲ ቅሪተ አካልን፣ ባህላዊ የቡና አፈላል ስነ-ስርዓትና ያሏትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በኤክስፖው በተሰጣት ስፍራ (ፓቪሊዮን) ለእይታ ማቅረቧንም ተናግረዋል።
በኤክስፖው የተሳተፉ 17 ድርጅቶች በሀገሪቱ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመጠቀም ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም 3 ሺህ 800 ሰዎች ደግሞ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ፍላጎት ማሳየታቸውን አስረድተዋል።
በኤክስፖው የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶች መጎብኘታቸውንም ገልፀዋል።
የኤክስፖው አዘጋጆች በዱባይ ካለው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ባህልና እሴት በሚያሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ቀንን ማክበራቸውን ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ አራት ወራትም በኤክስፖው የኢትዮጵያን ገፅታ እንዲሁም የኢንቨስትመንትና የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስተዋወቁ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የዱባይ ኤክስፖ 2020 ከተከፈተ ሁለት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 192 ሀገራት እየተሳተፉበት ይገኛል።
ከ25 ሚልየን በላይ ጎብኚዎች እንደሚጎበኙበት የሚጠበቀው የዱባይ 2020 ኤክስፖ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ የተከፈተ ሲሆን፤ እስከ መጋቢት 2014 ዓ.ም ለስድስት ወራት ቀጥሎ ይካሄዳል።
በአረብ ሀገራት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድ ለተነገረለት የዱባይ ኤክስፖ 2020 ከ10 ዓመት በላይ የፈጀ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።