ቴስላ በዱባይ የምድር ውስጥ መንገድ ሊገነባ ነው
ኤለን መስክ እንደ ላስ ቬጋስ አይነቱ የምድር ውስጥ መንገድ የዱባይን የትራፊክ መጨናነቅ ይቀርፋል ብለዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/13/273-170321-faef0d00-720_700x400.jpg)
የአለም መንግስታት ጉባኤ በዱባይ ሲካሄድ መስክ በበይነ መረብ ንግግር አድርገዋል
የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር እና ኩባንያው ቴስላ በአረብ ኤምሬትሷ ዱባይ የምድር ውስጥ መንገድ ሊገነቡ ነው።
"ድባይ ሉፕ" የሚል መጠሪያ የሚኖረው ፕሮጀክት በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ከተገነባው ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆንም ተገልጿል።
ኤለን መስክ በዱባይ በተካሄደው የአለም መንግስታት ጉባኤ የመጨረሻ ቀን ላይ በበይነ መረብ ንግግር ሲያደርጉ ነው ስለአዲሱ ፕሮጀክት ያብራራው።
የአረብ ኤምሬትስ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ሚኒስትር ኦማር አል ኦላማ፥ ቴስላ ከዱባይ ባለስልጣናት ጋር በመተባበር የምድር ውስጥ መንገዱን እንደሚገነቡ ገልጸዋል።
የምድር ውስጥ መተላለፊያው ወደአውሮፕላን ማረፊያ፣ ሆቴሎችና የተለያዩ መዳረሻዎች ያለምንም እንቅፋት በፍጥነት ለመድረስ ያስችላልም ማለታቸውን ዘናሽናል ኒውስ አስነብቧል።
የቴስላ ስራ አስፈጻሚው ኤለን መስክ በጉባኤው ባደረጉት ንግግር "የጋራ ፕሮጀክቱ መነሻና መዳረሻውን በዱባይ ህዝብ በብዛት የታጨቀባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል" ብለዋል።
"ልክ እንደ ትል ጉድጓድ ነው የሚሆነው፤ ከአንዱ የከተማዋ ክፍል ወደ አንዱ በቅጽበት ይደርሳሉ፤ ይህ አስደናቂ ነው፤ ይህን ትብብር እንፈልገዋለን" ሲሉም አክለዋል።
የዱባዩ የምድር ውስጥ መንገድ ከላስ ቬግስ ጋር እንደሚመሳሰል ተገልጿል።
ሁለት አመት የፈጀው የ"ላስ ቬጋስ ሉፕ" የአለማችን ግዙፍ የስብሰባ ማዕከል በሚገኝበት ስፍራ ምድር ውስጥ ነው የተሰራው።
70 ሾፌር አልባ ተሽከርካሪዎች የሚርመሰመሱበት የምድር ውስጥ መንገድ አምስት ጣቢያዎች አሉት። በቀጣይም ከአውሮፕላን ማረፊያ እና ሆቴሎች ጋር የሚያስተሳስሩ 100 ጣቢያዎች እንዲኖሩት ታቅዷል።
እንደ ላስ ቬጋስ ሁሉ በአለማችን ከፍተኛ ጎብኝዎች ያሏት ዱባይ የምድው ውስጥ መንገድ መገንባቷ የትራፊክ መጨናነቅን በእጅጉ እንደሚቀንስ ኤለን መስክ ተናግረዋል።
የምድር ውስጥ ትራንስፖርት ከመሬት በላይም ሆነ በበራሪ ድሮኖች ከሚሰጠው አገልግሎት በተለየ የአየር ንብረት ተጽዕኖ የማያገኘው መሆኑን በማንሳትም የቀጣዩ ትውልድ ቀዳሚው ምርጫ እንደሚሆን አብራርተዋል።