![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/13/258-142556-gettyimages-824340012-copy_700x400.jpg)
ሩሲያ በቀይ ባህር ላይ ወታደራዊ ማዘዣ ለመገንባት ጥያቄ ካቀረበች ስድስት ዓመት ሞልቶታል
ሩሲያ በቀይ ባህር ወታደራዊ ማዘዣ ለመገንባት ከሱዳን ጋር መስማማቷ ተገለጸ።
ሩሲያ ከቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር መንግሥት ጋር በቀይ ባህር ወታደራዊ ማዘዣ ለመገንባት ተስማምታ ነበር።
ይሁንና በሱዳን ያጋጠመው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሩሲያ ይህን ወታደራዊ ማዘዣ እንዳትገነባ እክል ፈጥሮባት ቆይቷል።
አሁን ላይ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያለችው ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ ዩሱፍ በሩሲያ ጉብኝት አድርገዋል።
ሚንስትሩ ከሩሲያ አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር በሞስኮ ተወያይተዋል።
ሚንስትሩ አሊ ዩሱፍ በሞስኮ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ "ሩሲያ ከሱዳን ጋር ባላት ስምምነት መሰረት በቀይ ባህር ወታደራዊ ማዘዣ ትገነባለች፣ ይህን ስምምነት እንዳይተገበር የሚከለክል ነገር ምንም የለም" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሩሲያ ከቀድሞውም ሆነ ከአሁኑ የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት ያላት ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በቅርቡ ፖርት ሱዳንን ጎብኝተዋል።
ባለፈው ዓመት የሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ሩሲያ ለሱዳን የጦር መሳሪያ ለመርዳት እና በምትኩ በቀይ ባህር ነዳጅ ማደያ ለመገንባት ጥያቄ ማቅረቧን ተናግረው ነበር።
ሱዳን ካለባት የእርስ በርስ ጦርነት ጫና በተጨማሪ በቀይ ባህር ላይ ባላት ቁልፍ ቦታ የሀያላን ሀገራት ሀይል ፍትጊያ አደጋ ተደቅኖባታል።
ከዚህ ባለፈም ሱዳን የወርቅ ማዕድን ሀብታም መሆኗ ምዕራባዊያን እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ትኩረትን ትስባለች።