ትራምፕ ከፑቲን ጋር በሳኡዲ ሊገናኙ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጡ
የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ምክክር የሳኡዲው ልኡል አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን እንደሚሳተፉበት ተገልጿል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/13/273-155504-trump-putin_700x400.jpg)
የአሜሪካና ሩሲያ መሪዎች በትላንትናው ዕለት ለ1፡30 ደቂቃ የፈጀ የስልክ ውይይት አድርገዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሳኡዲ አረብያ ተገናኝተው እንደሚመክሩ ተነግሯል፡፡
የዩክሬን ሩስያ ጦርነትን ማስቆም ላይ ትኩረቱን ያደርጋል የተባለው የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ውይይት የሳኡዲ አረብያው ልኡል አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን እንደሚሳተፉበት ተገልጿል፡፡
ልኡል አልጋወራሹ ከትራምፕ እና ፑቲን ጋር ያላቸው ጠንካራ ወዳጅነት ሪያድ የመሪዎቹን ውይይት እንድታስተናግድ ሳያስመርጣት እንዳልቀረ ተገምቷል።
ሞስኮ እና ሪያድ በአለም ነዳጅ ላኪ ሀገራት አባልነት ካላቸው ትብብር ባለፈ ሳኡዲ በዩክሬን ጦርነት የምርኮኞች ልውውጥን በማሸማገል ውጤታማ ስራ ሰርታለች፡፡
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከሩስያው አቻቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንት የስልክ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ሶስት አመት ገደማ ያስቆጠረውን የዩክሬኑን ጦርነት ለማቆም ከዩክሬኑ መሪ ጋር "በአፋጣኝ" ድርድር እንዲጀመር መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ትራምፕ ከስልክ ውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ጦርነቱ መቋጫውን በቅርቡ እንደሚያገኝ ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
የሰላም ድርድሩን ተጨባጭ ለማድረግ ዩክሬን አንዳንድ ግዛቶቿን ልታጣ እንደምትችል የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ አባልነት ጥያቄዋንም ማንሳት እንደሚኖርባት አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም መሪዎቹ አንደኛው በሌላኛው ሀገር ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ መስማማታቸውን የገለጹት ትራምፕ በቅርብ ጊዜ ዩክሬንን የመጎብኝት እቅድ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች በሳኡዲ እንደሚገናኙ ከመነገሩ ባለፈ ስለሚገናኙበት ቀን ይፋ የሆነ ነገር የለም። ትራምፕ በአሜሪካ አዳዲስ ፕሬዝዳንቶች ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ ቀዳሚ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን በሳኡዲ ለማድረግ ማቀዳቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው በፈረንጆቹ 2017 በተመሳሳይ የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን በሪያድ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ሩስያ እና ሳኡዲ ከአሜሪካ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በውጥረት የተሞላ ነበር፡፡
ትራምፕ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ቅድሚያ ከሰጧቸው ጉዳዮች መካከል የሚገኙትን የመካከለኛው ምስራቅ እና የዩክሬንን ጦርነት ማስቆምን ለማሳካት ከሞስኮ እና ሪያድ ጋር ይበልጥ በቅርበት ሊሰሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡