የአርጀንቲና እና ጀርመንን የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ሽንፈት ገምቶ የተሳካለት ቶቢ፥ እንደ ደቡብ አፍሪካው የአለም ዋንጫ "ፓል" ይሳካለት ይሆን?
በኳታሩ የአለም ዋንጫ ከታዩ አንፀባራቂ ኮከቦች አንዱ ቶቢ የተሰኘው ፔንጉይን ነው።
የ12 አመቱ ቶቢ የማይታመኑ የሚመስሉ ግምቶቹ እውን ሆነው ታይተዋል።
የሜሲ ሀገር አርጀንቲና በሳኡዲ አረቢያ እንደምትሸነፍ ገምቶ ተሳክቶለታል።
የዱባዩ ቶቢ፤ ጃፓን የአራት ጊዜ ሻምፒዮናዋን ጀርመን በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ታሸንፋለች ብሎ ሲገምት የተጠራጠሩት በርካታ ናቸው።
ይሁን እንጂ ጃፓን ከመመራት ተነስታ 2 ለ 1 በማሸነፏ የቶቢ ዝና እየጨመረ ሄዷል።
ስፔን ኮስታሪካን እንደምታሸንፍ የሰጠው ግምትም ተጠባቂ ቢሆንም ተሳክቶለታል።
በየቀኑ አሸናፊ ይሆናል ያለውን ሀገር ቡድን እየገመተ ያለው ፔንጉይን፤ አብዛኞቹ ግምቶቹም ስኬታማ ናቸው ተብሎለታል።
የቶቢ ተንከባካቢ አህመድ፥ "ሁሉም ፔንጉዌኖች ስል ናቸው፤ ቶቢ ግን ይለያል፤ በዙሪያው ያሉ ነገሮችን የሚያጤንበት መንገድም ግሩም ነው ብሏል።
ጨዋታ ወዳጁ ቶቢ ቀለማትን ይለያል፤ ትርኢት ሲቀርብም ቀልብ ሳቢው እሱ ነው።
በኳታሩ የአለም ዋንጫ እየሰጠ ያለው ግምትም የበርካቶችን አድናቆት እንዲያተርፍ አድርጎታል።
እንደ ቶቢ ሁሉ በደቡብ አፍሪካው የአለም ዋንጫ ፓል የተሰኘው ኦኮቶፐስ ከ14 ግምቱ 12ቱ ተሳክቶለት መነጋገሪያ እንደነበር ይታወሳል።
ኑሮውን በጀርመን ባህር ውስጥ ያደረገው ፓል የአለም ዋንጫውን ስፔን እንደምታነሳም ገምቶ አለምን አስደምሟል።
የኢራኑ የወቅቱ ፕሬዚዳንት አህመዲን ነጃድ ግን ፓል የምዕራባውያን ፕሮፖጋንዳ እና መጥፎ ልማድ ማስፋፊያ ነው በሚል ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው አይዘነጋም።
ገማቹ ፖል የ2010ሩ የአለም ዋንጫ ከተጠናቀቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ህይወቱ ቢያልፍም እነቶቢ ሌጋሲውን እያስቀጠሉ ነው።