በ0.35 ዶላር የተገዛው ሙዝ በጨረታ 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ተሽጧል
ጣሊያናዊው አርቲስት ሙዝ ከግድግዳ ጋር በፕላስተር አጣብቆና "ኮሜዲያን" የሚል ስያሜ ሰጥቶ ያቀረበው "የጥበብ ስራ" ከተጠበቀው በብዙ እጥፍ ከፍ ያለ ዋጋ አውጥቷል
ቻይናዊው የክሪፕቶከረንሲ ባለጠጋ ጀስቲን ሰን ከ6 ሚሊየን ዶላር በላይ ያፈሰሰበትን ሙዝ እንደሚበላው ተናግሯል
በአሜሪካዋ ኒውዮርክ ግድግዳ ላይ በፕላስተር የተለጠፈ ሙዝ በጨረታ 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር መሸጡ መነጋገሪያ ሆኗል፡።
ማውሪዚዮ ካቴላን የተባለ ጣሊያናዊ ለብዙዎች ስሜት የማይሰጥ የሚመስል ነገር ግን "ኮሜዲያን" የሚል ስያሜ የሰጠው የጥበብ ስራ ለጨረታ ቀርቧል።
የጥበብ ስራው ምንም የተለየ ነገር የለውም፤ አንድ ሙዝ ግድግዳ ላይ በፕላስተር የተጣበቀበት ነው።
ጣሊያናዊው የቪዡዋል አርቲስት ያቀረበው "የጥበብ ስራ" ግን ከተጠበቀው በላይ በአራት እጥፍ የላቀ ዋጋ ማውጣቱን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
ክሪፕቶከረንሲ ባለጠጋ ያደረገው ቻይናዊው ጀስቲን ሰን ስድስት ተጫራቾችን አሸንፎ ከ6 ሚሊየን ዶላር በላይ ያፈሰሰበትን ሙዝ ከፕላስተሩ አላቆ ራሱ እንደሚመገበው ተናግሯል።
ግድግዳ ላይ የተለጠፈው ሙዝ በአለማችን ውድ ዋጋ ያወጣው ፍራፍሬ ለመሆን በቅቷል።
6 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ያወጣው ሙዝ ከጨረታው ቀን ቀደም ብሎ ከገበያ በ0.35 ዶላር መገዛቱም ነው የተገለጸው።
በፕላስተር የተጣበቀው ሙዝ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ጥበብ ስራ ለህዝብ ይፋ የሆነው በ2019 ነበር። "የጥበብ ስራነቱ ምኑ ጋር ነው" የሚል ከፍተኛ መከራከሪያ ማስከተሉና በአለም ዙሪያ መነጋገሪያ መሆኑም ይታወሳል።
"ኮሜዲያን" ባለፉት አምስት አመታት በመላው አለም ሲዘዋወር ሙዙ ሲበላሽ እንዴት እንደሚቀየር መመሪያ ሰፍሮበታል።
ከግድግዳ ጋር በፕላስተር እንዲጣበቅ የተደረገው ሙዝ አለምን ሲዞር ከአንድም ሁለት ጊዜ ተበልቶ በሌላ ሙዝ ተተክቷል።
"ኮሜዲያን" በ2023 በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ሉም ሙዚየም ሲታይ አንድ የጥበብ ተማሪ ሙዙን ከፕላስተር አላቆ እንደበላው የሚታወስ ነው። ሙዚየሙም አዲስ ሙዝ ተክቶ የጥበብ ስራው መታየቱን ቀጥሎ ነበር።
የጣሊያናዊው አርቲስት የፈጠራ ውጤት በአሜሪካ ሚያሚ በ120 ሺህ ዶላር ከተሸጠ በኋላ አንድ የግለሰብ ሙዙን ከፕላስተሩ በማላቀቁ ቁጣ መቀስቀሱንም ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።