የስዊድኗ የጾታ እኩልነት ሚኒስትር “ከልክ ባለፈ የሙዝ ፍርሃት” ተጠቅተዋል ተባለ
ሚኒስትሯ በቢሯቸውም ሆነ ለጉብኝት በሚያመሩበት ስፍራ ሙዝ በፍጹም ማየት እንደሌለባቸው ማሳሰባቸውን አፈትልኮ የወጣ የኢሜል መልዕክታቸው አሳይቷል
“የሙዝ ፍርሃት” መነሻው ምን እንደሆነ እስካሁን ባይታወቅም ከልጅነት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ተገምቷል
የስዊድን የጾታ እኩልነት ሚኒስትር በአለማችን ባልተለመደው የፍርሃት አይነት ተጠቅተዋል።
ሚኒስትሯ ፓውሊና ብራንድበርግ ሙዝ መመገብ አይደለም ማየት ያርዳቸዋል።
ብራንድበርግ ለሙዝ ከልክ ያለፈ ፍርሃት ወይም “ፎቢያ” እንዳለባቸው ኤክስፕረሰን የተባለው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።
ሚኒስትሯ ባልደረቦቻቸው ሙዝ ይዘው ወደ ቢሮ እንዳይገቡ ማሳሰባቸውን አፈትልኮ ወጥቷል የተባለው የኢሜል መልዕክት ማመላከቱን ፖለቲኮ መጽሄት አስነብቧል።
ከቢሮ ውጭ ጉብኝት በሚያደርጉባቸው ስፍራዎችም ሙዝ ካለ በፍጥነት ከእይታቸው ውጪ እንዲሆን መልዕክቱ ያሳስባል ተብሏል።
የስዊድን ሊብራል ፓርቲ አባል የሆኑት የጾታ እኩልነት ሚኒስትሯ ሙዝ ሲመለከቱ ወይም ሲሸታቸው ሰውነታቸው እንደሚቆጣና የህክምና እርዳታ እንደሚሹ መናገራቸው ተዘግቧል።
ብራንድበርግ በ2020 በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ “የአለማችን ልዩው የፍርሃት (ፎቢያ) አይነት ተጠቂ ነኝ” ብለው ፍራፍሬው ከልክ ላለፈ ፍርሃት እንደሚዳርጋቸው ገልጸው ነበር። ይሁን እንጂ የኤክስ ልጥፉ ወዲያውኑ መነሳቱን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
ሌላኛዋ የስዊድን ፖለቲከኛ ቲሬሳ ካርቫልሆም “የሙዝ ፍርሃት” እንዳለባቸው በመግለጽ ለብራንድበርግ “ብችኛ አይደለሽም” የሚል መልዕክት አጋርተዋል።
ብዙም ያልተለመደው “የሙዝ ፍርሃት” ተጠቂዎች ፍራፍሬውን ሲመለከቱ አልያም ሲያሸቱ ሰውነታቸው በፍርሃት ይርዳል፤ የማስመለስና የማጥወልወል ስሜት ውስጥም ይገባሉ።
ለዚህ ችግር የሚዳርገው መንስኤ እስካሁን በጥናት ባይደረስበትም ባለሙያዎች በህጻንነት ሊገጥሙ ከሚችሉ መጥፎ ትዝታዎች ጋር ሊያያዝ እንደሚችሉ ይገመታሉ።