ክሱ በአሜሪካ የተመሰረተ ነው
አሜሪካ የ145 ሚሊዮን ዜጎቼን መረጃ መዝብረዋል ባለቻቸው አራት ቻይናዊያን ላይ ክስ መሰረተች
አሜሪካ በግዙፉ ኩባንያ ኢኪዩፋክስ /Equifax/ ላይ በፈረንጆቹ 2017 የሳይበር ጥቃት አድርሰዋል ባለቻቸው 4 የቻይና መከላከያ ሰራዊት ባልደረቦች ላይ ክስ መሰረተች፡፡
በ2017 በተከሰተው እና የአሜሪካንን ከፍተኛ ባለስልጣናት ዒላማ አድርጎ ተፈጽሟል በተባለለት በዚህ ግዙፍ የመረጃ ጥቃት ተግባር እጃቸው አለበት የተባሉ አራት የቻይና መከላከያ አባላት ላይ ትላንት ሰኞ ክስ መመስረቷ ተነግሯል፡፡
አራቱ የቻይና የመከላከያ ባልደረቦች በአሜሪካ ግዙፍ የብድር አቅርቦት ኤጀንሲ ኢኪዩፋክስ ላይ ፈፅመዋል በተባለው የሳይበር ጥቃት ነው የተከሰሱት፡፡
በጥቃቱ የ145 ሚሊዮን አሜሪካዊያን የግል መረጃዎችን እና ሚስጥራዊ የንግድ ሰነዶች ተመዝብረዋል፡፡
በአይነቱ ግዙፍ በሆነው የሳይበር ጥቃት ግማሽ የሚሆኑ አሜሪካዊያን ሰለባ የሆኑ ሲሆን በጥቃቱ ስሞች፣ የትውልድ ቀን፣ የማህበራዊ ዋስትና ቁጥሮች፣ ዝርዝር የጤና ሁኔታ እና የባንክ አካውንት ይገኙበታል፡፡
የመረጃ ጥቃቱ ከመድረሱ አንድ ወር ቀደም ብሎ መንግስት ለተቋሙ ማስጠንቀቂያ እንደሰጠው የተነገረ ሲሆን ኢኪዩፋክስ ክፍተቱን መሙላት ባለመቻሉ ነው የጉዳቱ ሰለባ የሆነው፡፡
ኩባንያው በወቅቱ ከፍተቱን ቢሞላ እጅግ ግዙፍ የሚባለውን የሳይበር ጥቃት ማስቀረት ይችል እንደነበር የ2018 የአሜሪካ ምክር ቤት ጥናት ማመልከቱን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡