8 ሺህ የቦስኒያ ሙስሊሞች የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል
ሆላንድ በሰርቢያ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ይቅርታ ጠየቀች፡፡
ከ27 ዓመት በፊት የባልካን ጦርነት መከሰቱን ተከትሎ ነበር የበርካታ ሀገራት ጦር አባላት የሰላም አስከባሪ ሀይላቸውን ወደ ሰርቢያ እና አካባቢው የላኩት፡፡
የሰርቢያ ቦስኒያ ጦርም በወቅቱ 8 ሺህ የቦስኒያ ሙስሊም ዜጎችን ለይቶ ያጠቃ ሲሆን፤ ድርጊቱ በተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑ ተደንግጓል፡፡
በወቅቱ ጦራቸውን ወደ ሰርቢያ ከላኩ ሀገራት መካከል ሆላንድ ወይም ኔዘርላንድ አንዷ ስትሆን፤ በወቅቱ የተፈጠረውን የዘር ማጥት ወንጀል ማስቆም አልቻልንም በሚል ይቅርታ ጠይቃለች፡፡
ሆላንድ ይቅርታ የጠየቀችው የቦስኒያ ሙስሊሞችን እና የሟች ቤተሰቦችን እንደሆነ የሆላንድ መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የሆላንድ መከላከያ ሚኒስትር ካጅሳ ኦሎንገሬን እንደተናገሩት የቦስኒያ ሙስሊሞችን ጭፍጨፋ የፈጸመው የቦስኒያ-ሰርብ ጦር ቢሆንም እኛን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስጣል ነበረበት ብለዋል፡፡
የሆላንድ ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት ለቦስኒያ ሙስሞች ጭፍጨፋ በከፊል ሆላንድን ጥፋተኛ ያለ ሲሆን፤ ለተጎጂዎች ካሳ ሊከፈል እንደሚገባ አሰውቆ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የዘር ማጥፋት ወንጀሉ በተፈጸመበት ወቅት የሆላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊም ኮክ ድርጊቱ ጥፋት መሆኑን ጠቅሰው ይቅርታ መጠየቅ ግን አይጠበቅብንም ሲሉ ምላሽ ሰጥተውም ነበር፡፡
የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ከፈረንጆቹ 1992 እስከ 1995 ድረስ በዓለማችን አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ያስተናገደች ሲሆን 100 ሺህ ሰዎች በዚሁ ጦርነት ምክንያት ተገድለዋል፡፡