ሂሳብ ላለመክፈል የሚያንቀጠቅጥ በሽታ ያለባቸው የሚመስሉት ሆላንዳዊ…
ለአመታት ምግብ ቤቶችን ያማረሩት የ58 አመቱ አዛውንት በመጨረሻም የማምለጫ ስልታቸው ተደርሶበታል

አዛውንቱ ሀሰተኛ ዘዴያችውን ተጠቅመው በጥቂቱ ከ127 ጊዜ በላይ ሂሳብ ሳይከፍሉ ለመውጣት መሞከራቸውን ፖሊስ ገልጿል
በሆላንዷ ዴፍት ከተማ የሚገኙ አብዛኞቹ ምግብ ቤቶች የ58 አመቱን አዛውንት ያውቋቸዋል።
እኝህን አዛውንት ታዋቂ ያደረጋቸውም ምግብም ሆነ መጠጥ ተጠቅመው ሂሳብ ሳይከፍሉ ለመውጣት የሚፈጥሩት ድራማ ነው።
ምግብ ቤቶቹ አዛውንቱ የሚጠቀሙት ስልት መደጋገሙ ቢያሰለቻቸውም የሚመለከቱት ነገር የሀሰት መሆኑን መጠራጠር የሚከብዳቸውም ጥቂቶች አልነበሩም።
ባለፈው ወር ግን በአንድ ምግብ ቤት የገጠመው ክስተት አዛውንቱ ለአመታት ሲያታልሉ መክረማቸውን አመላክቷል።
ማይክ ሆጌቪን የተባለ አስተናጋጅ እንደሚለው አዛውንቱ ምግብ ካዘዙ በኋላ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችን እንብላ እያሉ የመጋበዝና ሁሉንም በፍጥነት ወዳጅ ለማድረግ የመሞከር ልማድ አላቸው።
ምግባቸውን በልተው ካጠናቀቁ በኋላ ሂሳብ ከመጠየቃቸው በፊት ግራ እጃቸውን ማንቀጥቀጥ ይጀምሩና የስትሮክ በሽታ እንዳለባቸው ይገልጻሉ።
በቅርቡ ይህን የተለመደ ስልታቸውን በመጠቀም ሂሳብ ሳይከፍሉ ለመውጣት ሲሞክሩ ግን የአንድ ምግብ ቤት ስራ አስኪያጅ የህክምና ባለሙያዎችን ይጠራል።
ባለሙያዎቹ ያደረጉት ምርመራ የ58 አመቱ አዛውንት የስትሮክ በሽታ እንደሌለባቸው ያሳየ ነበር፤ ወደ ሆስፒታል ወስደንዎት ተጨማሪ ምርመራ እናድርግልዎ ሲሏቸውም አሻፈረኝ ይላሉ።
108 ዶላር የሚያወጣ ምግብ የበሉት አዛውንት ሂሳቡን ሌላ ጊዜ እንዲከፍሉ ስምና አድራሻቸውን ሲጠየቁም የተሳሳተ መረጃ መስጠታቸውን ከህክምና ባለሙያዎቹ አንዱ በመግለጹ ፖሊስ ተጠርቷል።
ፖሊሶች የአዛውንቱን ኪስ ሲፈትሹም የተለያዩ ምግብ ቤቶች ለፖሊሶች በተደጋጋሚ የሚጠቁሙት ስም መሆኑ ተደርሶበታል ይላል የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ።
ግለሰቡ ይህንኑ ስልታቸውን ተጠቅመው በጥቂቱ 127 ጊዜ ሂሳብ ሳይከፍሉ ለመውጣት መሞከራቸውን ፖሊስ ጥቆማ እንደደረሰውም ነው የተገለጸው።
“የደች ምግብ ቤቶችን ያማረሩት አዛውንት” በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ክስ ተመስርቶባቸዋል ወይ የሚለው ግን አልተጠቀሰም።
በስፔን ኮስታ ብላንካ ክልል የልብ ህመም ያለበት በማስመሰል ከ20 በላይ ምግብ ቤቶችን ያታለለው ወጣትም ባለፈው አመት በቁጥጥር ስር መዋሉን ዘገባው አስታውሷል።