በሀገሪቱ ውሻን ለቤት እንስሳነት መጠቀም ባለፉት አመታት የጨመረ ሲሆን ከአራት ኮሪያ ቤተሰቦች አንዱ ውሻን በቤት እንስሳነት ይንከባከባል
ደቡብ ኮሪያ የውሻ ስጋ ለምግብነት እንዳይውል በህግ አገደች።
የደቡብ ኮሪያ ፖርላማ የውሻ ስጋ ለምግብነት እንዳይውል የሚከለክለውን ህግ ማጽደቁን ሮይተርስ ዘግቧል።
ህጉ በሀገሪቱ ለምዕተ አመት የቆየውን እና አውዛጋቢውን ልምድ ያስቆማል ተብሏል።
በአንድ ወቅት የውሻ ስጋን መብላት ከባድ በሆነው የደቡብ ኮሪያ የክረምት ወራት ጥንካሬን ያስገኛል የሚል እምነት ነበር።ነገረግን ይህ ልምድ አልፎ አልፎ የሚተገበር፣ በእድሜ ከፍ ያሉ ሰዎች እና በተወሰኑ ምግብ ቤቶች የሚዘወተር እየሆነ መጥቷል።ይህ የሆነው ብዙ ኮሪያውያን ውሻን የቤት እንስሳ በማድረጋቸው እና ውሾች የመታረዱበት መንገድ ከፍተኛ ትችት ማምጣቱን ተከትሎ ነው።
አርቢዎች እና ነጋዴዎች ውሾች የሚታረዱበት መንገድ እየተሻሻለ መምጣቱን ቢገልጹም፣ አክቲቪስቶች በኤሌክትሪክ ወይም ተሰቅለው ከሞቱ በኋላ መታረዳቸው አግባብ አይደለም የሚል ትችት ያቀርባሉ።
የውሻ ስጋ ለምግብነት እንዳይውል የሚደረገው ድጋፍ፣ ስድስት ውሾች እና ስምንት ድመቶች ባሏቸው የእንስሳት አፍቃሪ በሆኑት ፕሬዝደንት ዩን ሱክ ይኦል የስልጣን ዘመን ጨምሯል።
በሀገሪቱ ውሻን ለቤት እንስሳነት መጠቀም ባለፉት አመታት የጨመረ ሲሆን ከአራት ኮሪያ ቤተሰቦች አንዱ ውሻን በቤት እንስሳነት ይንከባከባል።
በገዥው ፖርቲ የቀረበው ይህ ረቂቅ ህግ በ208 አብላጫ ድምጽ ድጋፍ እና በሁለት ድምጸ ተአቅቦ ጸድቋል።
የውሻን ስጋ ለምግብነት ማዋልን የሚከለክለው ህጉ ከሶስት አመት የእፎይታ ጊዜ በኋላ ተግባራዊ ይደረጋል።
ለምግብነት ውሻን ማርባት እና ማረድ በሶስት አመት እስራት ወይም 22ሺ ዶላር እንደሚያስቀጣ ህጉ አስቀምጧል።
ይህ ረቂቅ ህግ ሲቀርብ ውሻ በማርባት የሚተዳደሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አርቢዎች እና የውሻ ስጋን የሚያቀነባብሩ ኢንዱስትሪዎች ተቃውመውታል።