ድርጅቱ አገልግሎቱን ላለፉት 20 ዓመታት በመስጠት ላይ ቢሆንም ከሰሞኑ ምስሉ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መሰራጨቱን ተከትሎ ብዙዎች ወደውታል ተብሏል
በቻይና ያለ አንድ ካፍቴሪያ ለደንበኞቹ ምግብ ከማቅረብ በተጨማሪ ፈቃደኛ እና ፍላጎቱ ላላቸው ደንበኞቹ ጸጉራቸውን በሻምፖ እንደሚያጥብ አስታውቋል፡፡
ይህ ካፍቴሪያ ከሰሞኑ በአንድ ደንበኛው አማካኝነት የሚሰጠው አገልግሎት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ መለቀቁን ተከትሎ በርካታ ቻይናዊን አድናቆታቸውን እየገለጹለት ይገኛሉ፡፡
ድርጅቱ ይህን አገልግሎት ላለፉት 20 ዓመታት በመስጠት ላይ ቢሆንም ከሰሞኑ ግን የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችሏል፡፡
ሀይዲላኦ የተሰኘው ይህ ካፍቴሪያ ታማኝ እና ፍላጎቱ ላላቸው ደንበኞቹ ጸጉራቸውን የሚያጥበው የምግብ ሽታ በልብሳቸው እና ጸጉራቸው ላይ እንዳይቀር በማሰብ ነው ተብሏል፡፡
ካፍቴሪያው አገልግሎቱን ሲሰጥ የሚሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች መለቀቃቸው ሌሎች አቻ ምግብ ቤቶች እና ካፍቴሪያዎች በመልካም ልምድነት ሊወስዱት እና ሊፎካከሩት እንደሚችሉም ተሰግቷል፡፡
የእስያ ምግቦች ለምግብ ማጣፈጫነት በዛ ያሉ ቅመሞችን በመጠቀም የሚታወቁ ሲሆን የምግብ ሽታዎች በልብስ እና እጅ ላይ እንደሚቀሩ ይገለጻል፡፡
ይህ ካፍቴሪያ የደንበኞቹን ችግር በመረዳት በሻምፖ ጽድት አድርጎ ጸጉርን፣ ፊት እና እጆችን ማጠቡ ተወዳጅ አድርጎት ቆይቷል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡