የፈረንሳይና የአረብ ኢምሬት ኩባንያዎች የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ተገለፀ
ኦሬንጅና ኢ የተሰኙ አለም አቀፍ ኩባንያዎች የኢትዮ ቴሌኮም የ45 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ሊወዳደሩ ይችላሉ ተብሏል
መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮምን የ45 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል
የፈረንሳይ እና የአረብ ኢምሬት የቴሌኮም ኩባንያዎች የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ፋይናንስ ሚንስቴር የኢትዮ ቴሌኮምን የ45 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል።
መንግሥት በቅርቡ ባወጣው ተጨማሪ መግለጫ ደግሞ ተጫራች ኩባንያዎች የግዥ ፍላጎታቸውን እስከ ቀጣዩ መስከረም ድረስ እንዲያስገቡለት ጠይቋል።
በዚህ መሰረትም የፈረንሳዩ ኦሬንጅ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ቴሌኮም ኩባንያ የሆነው ኢ ኤንድ የተሰኘው ተቋም የኢትዮ ቴሌኮምን የ45 በመቶ ድርሻ ለመግዛት የመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው ብሉምበርግ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ የመንግስት ድርሻ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮምን ለመሸጥ ከወሰነች የቆየች ቢሆንም በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ጦርነት እንዳዘገየውም ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለም ኢትዮጵያ ካሳፋሪ ኮም እና ኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ ሶስተኛ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ፈቃድ የመስጠት እቅድም አላት ተብሏል።
በአፍሪካ ካሉት የቴሌኮም ኩባንያዎች መካከል ሙሉ ለሙሉ የመንግስት ንብረት የሆነው ኢትዮ ቴሌኮምን ለመግዛት ሌሎች ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች በጨረታው የመወዳደር ፍላጎት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
በተለይም በኢትዮጵያ ሰፊ የህዝብ ብዛት መኖር፣ የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎት እየጨመረ መሄድ እና አገልግሎቱ አለመስፋፋቱ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት በድሬዳዋ የመጀመሪያውን የቴሌኮም አገልግሎት የጀመረ ሲሆን አገልግሎቶቹን ወደ ሁሉም የሀገሪቱ ቦታዎች በማስፋፋት ላይ መሆኑንም አስታውቋል።