የቴሌብር ደንበኞች 27 ነጥብ 2 ሚሊየን የደርሰ ሲሆን በ6 ወራት ውስጥ 161 ሚሊየን ብር በላይ ተንቀሳቅሷል
ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት 33 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ።
የደንበኞቹ ቁጥር 70 ሚሊየን መድረሱን ያስታወቀው ኩባንያው፥ የስድስት ወራት ስራ አፈጻጸም ሪፖርት አውጥቷል።
የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ19 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ኢትዮ ቴሌኮም ለአል ዐይን በላከው ሪፖርት አመላክቷል።
ከተገኘው ገቢ ውስጥ የሞባይል ድምጽ 47 ነጥብ 4 በመቶውን በመያዝ ሲመራ የኢንተርኔት አገልግሎት በ28 በመቶ ይከተላል።
ባለፉት ስድስት ወራት ከአለም አቀፍ አገልግሎት 64 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉም ነው የተመላከተው።
ከሃምሌ 2014 እስከ ታህሳስ 2015 ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ተጨማሪ 9 ነጥብ 2 ሚሊየን ደንበኞችን ያፈራው ኩባንያው፥ ጠቅላላ ደንበኞቹ 70 ሚሊየን መድረሳቸውን በመግለጫው ጠቁሟል።
የዲጂታን የፋይናንስ ስርአቱን እያገዘ የሚገኘው ቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥርም 27 ነጥብ 2 ሚሊየን መድረሱ ተገልጿል።
በስድስት ወራት ውስጥም በዚሁ አገልግሎት 166 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር መንቀሳቀሱ ነው የተነገረው።
ቴሌብርን ከ18 ባንኮች ጋር የማስተሳሰሩ ስራ መጠናቀቁንና በ15 ባንኮች ከባንኮች ወደ ቴሌብር እና ከቴሌብር ወደ ባንኮች ገንዘብ ማዘዋወር መቻሉንም መግለጫው አውስቷል።
ባለፉት ስድስት ወራት ቴሌብርን ከአለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊዎች ጋር ለማስተሳሰር ጥረት ተደርጎም ከ44 ሀገራት ዜጎች 714 ሺህ ዶላር በዚሁ አማራጭ ገንዝብ መላካቸውን ነው ኢትዮ ቴሌኮም በመግለጫው ያነሳው።
ኩባንያው በግማሽ በጀት አመቱ 60 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር እዳ መመለሱንም አስታውቋል።