የኢትዮ ቴሌኮምን 40% ድርሻ መግዛት የሚፈልጉ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ተጠየቀ
በግዢ ሂደቱ መሳተፍ የሚፈልጉ ኩባንያዎች ከሰኔ 8 ጀምሮ ለ30 ቀናት ፍላጎታቸውን ማሳወቅ ይችላሉ
ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር ዝግጅት መጠናቀቁን የገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል
የገንዘብ ሚኒስቴር እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር ኤጀንሲ እንዲሁም የኢትዮ-ቴሌኮም የቦርድ አመራሮች ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ምዕራፍ የተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮምን 40% ድርሻ ለመሸጥ ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን መግዛት የሚፈልጉ የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያዎች የፍላጎት መግለጫ (Expression of Interest - EOI) ከነገ ማክሰኞ ሰኔ 08 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ማስገባት እንደሚችሉ የኢትዮጵያ መንግስት አሳውቋል፡፡
የፍላጎት መግለጫው ለአንድ ወር የሚቆይና ዝርዝሩም በገንዘብ ሚኒስቴር እና በመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ድረ ገጽ ላይ እነደሚለቀቅ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ይርጋ ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ እንዳስታወቀው ፣ የፍላጎት መግለጫው ለሰላሳ ቀናት የሚቆይ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተወዳዳሪ ባለሀብቶች ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል በማዛወር ሂደት ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ቀረቦላቸዋል፡፡
ሂደቱን በማማከር ረገድ ‘ዴሎይት’ እንደ ዋና የግብይት አማካሪ ሆኖ የሚሰራ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
የመወዳደሪያ ፍላጎት መግለጫውን ተከትሎ ተጫራቾች የመወዳደሪያ ዕቅድ ጥያቄያቸውን (Request for Proposal - RFP) የሚያስገቡ ሲሆን አጠቃላይ ሂደቱም ወቅቱን በጠበቀ ቀልጣፋ አሰራረርን እንደሚገለጽ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም እ.አ.አ በ2018 የመንግስት ልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዞር በተያዘው እቅድ ውስጥ ከተካተቱ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮቴሌኮምን 5 በመቶ ድርሻ ለኢትዮጵያ ዜጎች ፣ 40 በመቶውን ደግሞ ለሁለት የውጭ ኩባንያዎች እንደሚሸጥ ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል፡፡