የፈረንሳዩ ኦሬንጅ የቴሌኮሙንኬሽን ኩባንያ የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት እንዳው አሳወቀ
ኦሬንጅ ኩባንያ ከ100 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ሀብት ያለው ተቋም ነው
ድርጅቱ በ26 አገራት ከ250 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አሉት
የፈረንሳዩ ኦሬንጅ የቴሌኮሙንኬሽን ኩባንያ የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ፍላጎትን ማሳወቁ ተገለጸ።
ኢትዮጵያ የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ መግዛት የሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን ከሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቁ መጠየቋ ይታወሳል።
በዚህ መሰረትም የቀድሞው ፋራንስ ቴሌኮም የአሁኑ ኦሬንጅ ቴሌኮም ኩባንያ የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመግዛት በይፋ ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል።
በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሔኖክ ተፈራ ከዚህ ኩባንያ ከፍተኛ አመራሮች ጋር መወያየታቸውን በትዊተር ገጻቸው ጠቅሰዋል።
አምባሳደሩ እንዳሉትም “በኢትዮ-ቴሌኮም ካፒታል ውስጥ ለመግባት በይፋ ካሳወቀው ኦረንዥ (ቴሌኮም) ኃላፊዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገናል” ብለዋል።
“ኢኮኖሚዋና ገቢዋ በፍጥነት በማደግ ላይ የምትገኘውና ከ100 ሚሊየን ህዝብ በላይ ያላት አገራችን በውጭ ባለሀብቶች ዘንድ ያላት ተፈላጊነት እንደቀጠለ ነው” ሲሉም አምባሳደሩ አክለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር ዝግጅት መጠናቀቁን የገንዘብ ሚኒስቴር ከዚህ በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።
የገንዘብ ሚኒስቴር እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር ኤጀንሲ እንዲሁም የኢትዮ-ቴሌኮም የቦርድ አመራሮች ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ምዕራፍ የተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን መግዛት የሚፈልጉ የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያዎች የፍላጎት መግለጫ (Expression of Interest - EOI) ከሰኔ 08 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ማስገባት እንደሚችሉ አሳውቆ ነበር።
የፍላጎት መግለጫው ለአንድ ወር እንደሚቆይ በወቅቱ የተገለጸ ሲሆን፤ የፍላጎት ማስገቢያ ቀኑ ባሳለፍነው ሳምንት የተጠናቀቀ ቢሆንም መንግስት የፍላጎት መግለጫውን ጊዜ ስለመጠናቀቁ ወይም መራዘሙ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
በዚህ የኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ግዥ ሂደት ሌሎች የአውሮፓ እና አስያ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን እንደሚያስገቡ ቢጠበቅም አስካሁን ከፈረንሳዩ ኦሬንጅ ኩባንያ ውጪ ፍላጎቱን ያሳወቀ ኩባንያ ይኑር አይኑር እስካሁን መንግስት አልተናገረም።
ኢትዮ ቴሌኮም እ.አ.አ በ2018 የመንግስት ልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዞር በተያዘው እቅድ ውስጥ ከተካተቱ ድርጅቶች አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮቴሌኮምን 5 በመቶ ድርሻ ለኢትዮጵያ ዜጎች ፣ 40 በመቶውን ደግሞ ለሁለት የውጭ ኩባንያዎች እንደሚሸጥ ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል።
የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ጥያቄ ያቀረበው ኦሬንጅ ኩባንያ ከ33 ዓመታት በፊት ፍራንስ ቴሌኮም በሚል የተመሰረተ ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙንኬሽን ተቋም ነው።
የድርጅቱ 23 በመቶ የፈረንሳይ መንግስት ደርሻ ሲሆን ቀሪው የተለያዩ የግል ኩባንያዎች እና ሌሎች ህዝባዊ ተቃማት ድርሻ መሆኑን ከድርጅቱ ድረገጽ ላይ የገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ኦሬንጅ ኩባንያ አሁን ላይ ፈረንሳይን ጨምሮ በአውሮፓ፤መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ የቴሌኮሙንኬሽን አገለግሎት በመስጠት ላይ ሲሆን አጠቃላይ የድርጅቱ አጠቃላይ ሀብትም ከ100 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ነው።
ድርጅቱ እስከ ፈረንጆቹ 2020 ድረስም በ26 የዓለማችን አገራት ከ250 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ200 ሚሊዮን በላይ ያህሉ የሞባይል ደንበኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የብሮድባንድ ተጠቃሚዎች ናቸው።