በአፋር ክልል የርእደ መሬት አደጋ ተከስቶ እንደነበር ተገለጸ
በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 3 ሆኖ የተመዘገበው አደጋ ከአዲግራት በ56 ኪሎሜትር ወደ ዳሎል አቅጣጫ ነው የደረሰው
ከዚህ ርዕደ መሬት ከስአታት በኋላም በዳህላክ ደሴት ተመሳሳይ አደጋ ተከስቷል ተብሏል
በአፋር ክልል የርእደ መሬት አደጋ ተከስቶ እንደነበር ተገልጿል።
በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 3 ሆኖ የተመዘገበው አደጋ ከትናንት በስቲያ ታህሳስ 17 2015 ከቀኑ 9 ስአት ከ21 ደቂቃ ላይ ተከስቶ እንደነበር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገልጿል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ፣ ስፔስ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተሩ ዶክተር ኤልያስ ለዊ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ርዕደ መሬቱ ከአዲግራት በ56 ኪሎሜትር ወደ ዳሎል አቅጣጫ መከሰቱን ተናግረዋል።
“የአሜሪካ ጂዮሎጂካል ሰርቬይ መረጃ የመሬት መንቀጥቀጡ ከአዲግራት 37 ኪሎሜትር ርቀት ላይ መድረሱን ቢገልጽም ከሶስት ጣቢያዎች የሰበሰብናቸው መረጃዎች አደጋው አፋር በርሃ ውስጥ መከሰቱን አረጋግጠዋል” ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ታህሳስ 17 2015 ዓ.ም፣ ከምሽቱ 1 ስአት ከ20 ላይም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር ተመሳሳይ አደጋ መመዝገቡን የአሜሪካ ጂዮሎጂካል ሰርቬይ ያወጣው መረጃ ያሳያል።
ዶክተር ኤልያስ ግን “የኛ ጣቢያዎች መረጃ አደጋው የዳህላክ ደሴት አካባቢ ላይ እንደደረሰ ያሳያል” ነው ያሉት።
በዳህላክ የደረሰው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 4 ሆኖ መመዝገቡንም ተናግረዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን እያጠናቀርን እንገኛለን ያሉት ዳይሬክተሩ፥ በአፋርም ሆነ በዳህላክ በደረሱት አደጋዎች የከፋ ጉዳት ይደርሳል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።
ምክንያታቸው ደግሞ በተለይ በአፋር የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በርሃ ውስጥ ሰዎች በማይኖሩበት አካባቢ መሆኑ ነው።
ይህን መሰል አደጋ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ቢደርስ ግን እጅግ ከባድ ውድመት እንደሚያስከትልም አብራርተዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ የከፋ ጉዳት ያስከተል ርዕደ መሬት ባታስተናግድም ደጋግሞ ጎብኝቷታል።
የመጀመሪያው የተመዘገበው ርእደ መሬት በፈረንጆቹ በ1906 ነሐሴ 25 ቀን መከሰቱን መረጃዎች ያወሳሉ።
በዚህ በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 8 ሆኖ በተመዘገበ ርዕደ መሬት የደረሰው ጉዳት ባይጠቀስም በወቅቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እጅግ ተረብሸው እንደነበርም ይነገራል።
በ1953 ካራቆሬ ተበሎ በሚጠራ አካባቢ የተከሰተው መሬት መንቀጥቀጥ እስካሁን ከተመዘገቡት ሁሉ ከፍተኛውን ጉዳት ያስከተለ ነው።
በሬክተር ስኬል 6.5 የተመዘገበው አደጋ በጥቂቱ የ30 ሰዎችን ህይወት መቀማቱ ተዘግቦ ነበር።