ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን እንዴት ይመራሉ? ማድረግ ያለባቸው ጥንቃቄስ ምንድን ነው?
ዝነኛ ወይም ታዋቂ ሰዎች ህይወታው ሲያለልፍ ብዙዎቻችን የተለያዩ ስሜቶችን እናስተናግዳለን
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ዝነኛ ወይም ታዋቂ ኢትዮጵያዊያንን በድንገት ህይወታቸው እያለፈ ይገኛል
ህይወታቸው ያለፉ የዝነኛ ኢትዮጵያዊያን ሞት መንስኤ ምርመራ ወደፊት ይገለጻል ቢባልም ሪፖርቱ ለህዝብ ይፋ አለመደረጉ ከነዚህ ሰዎች ህይወት ሊገኝ የሚገባው ትምህርት እየተገኘ አይደለም።
ብዙ አድናቂዎች ያሏቸው እነዚህ ዝነኞች ህይወታቸው በድንገቱ እያለፈ መሆኑን ተከትሎ ከመሞታቸው በፊት ምን አይነት ግላዊ ህይወት ኖሯቸው ይሆን? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ነው።
ዝነኝነታቸው የግል እና ማህበራዊ መስተጋብራቸውን በማይጎዳባቸው መልኩ የሚያስኬዱ ብዙ ታዋቂ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ህይወታቸውን ለአደጋ በሚያግልጥ መልኩ የሚመሩ ታዋቂ ሰዎችም ይኖራሉ።
ዓልዓይን አማርኛ በተለይም ዝነኛ ወይም ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን እንዴት ይመራሉ? ማድረግ ያለባቸው ጥንቃቄስ ምንድን ነው? እና ሌሎችንም ጉዳዮች ለማየት ሞክሯል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የሹፍርና ባለሙያ እንደነገረን ከሆነ ከአዲስ አበባ ውጪ በሆኑ ቦታዎች ለፊልም፣ሙዚቃ እና ለሌሎች የኪነጥበብ ስራዎች በሚል ሙያተኞችን ከቦታ ቦታ ያጓጉዛል።
ይህ የሹፍርና ባለሙያ በነዚህ ጉዞዎች ወቅት የታዘበውን ሲነግረን "ሙያቸውን አክብረው የሚሰሩ ብዙ ዝነኛ ስዎች ቢኖሩም፣ እንዲህ ያደርጋሉ ተብለው ሊገመቱ የማይችሉ፣ ህዝቡ ጋር ያላቸው ዋጋ ከፍ ያለ እና ብዙ ታዳጊዎች በአርዓያነት የሚያዩዋቸው ዝነኞች ብዙ አስነዋሪ ነገሮችን ሲፈጽሙ ተመልክቻለሁ" ብሏል።
እነዚህ ዝነኞች ከሚፈጸሟቸው አስነዋሪ ድርጊቶች መካከል ብዙ የለፉበትን ታዋቂነታቸውን እና ተወዳጅነታቸውን ሊጎዱ የሚችሉ ናቸውም ብሏል ይህ አስተያየት ሰጪ።
የስነ ልቦና አማካሪው አቶ ዮፍታሄ አሰግድ ዝነኞች ወይም ታዋቂ ሰዎች ህይወታቸውን ለመለወጥ የለፉበት ፍሬ እነዚህ ሰዎች ለሀገር ሊያበረክቱት ስለሚችሏቸው እድሎች ሲሉ ለህይወታቸው ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።
ታዋቂ ሰዎች ታዋቂ ካልሆኑ ሰዎች ያነሰ ነጻነት አላቸው የሚሉት አማካሪው በተለይም እንደ ሰው የፈለጉትን ነገር ለማድረግ ስለሚቸገሩ የበለጠ ጫና ውስጥ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።
ከአድናቂዎች የሚመጡ ጭብጨባዎች፣ ትኩረት እና ሌሎች ተያያዥ ድርጊቶች በራሳቸው ላይ የስነ ልቦና ጫና እንደሚፈጥሩም አቶ ዮፍታሄ ጠቁመዋል።
ዝነኞች ከአድናቂዎቻቸው የሚቀበሉት አክብሮት እንደ ታዋቂ ሰዎቹ የአዕምሮ አረዳድ ስለሚለያይ ምላሻቸውም በዛው ልክ ሊራራቅ ይችላልም ተብሏል።
የታዋቂ ሰዎች ውጪያዊ እና የቤት ውስጥ ባህሪያት ወይም ድርጊት ተመሳሳይ አለመሆን እና ዝነኛው ሰው በአድናቂዎቹ አዕምሮ ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን አቀባበል ሲያስብ እና በትክክል እየኖረ ያለውን ህይወት ሲያነጻጽር ወደ ድብርት አልያም ለሌሎች የአዕምሮ ህመሞች ሊዳረጉ ይችላሉም ብለዋል።
አድናቂዎች ያደነቁትን ግለሰብ ግላዊ ነጻነት እንዲሰጡ ፣እንዲያከብሩ እና እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን እንዲረዱም ባለሙያው አሳስቧል።
አቶ ዮፍታሄ አክለውም ጥቂት ታዋቂ ሰዎች የጤና፣ የገንዘብ፣ የሚዲያ እና እንደየ አስፈላጊነቱ በሌሎች ጉዳዮች የሚያማክሯቸው ባለሙያዎች እና ተቋማት ቢኖሩም ብዙዎቹ ግን ይህን እያደረጉ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።
ታዋቂ ሰዎች ከዚህ ባለፈ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ገድብ ማስቀመጥ፣ አካባቢያዊ ውግንናን ከሚያንጸባርቁ እና ቃለ መጠይቆችን ሲሰጡም የሚዲያ ተቋማቱን ማንነት እንዲሁም ፖለቲካዊ ወገንተኝነታቸውን ከሚያሳዩ ሚዲያዎች ሊርቁ እንደሚገባም አሳስበዋል።