በቱርክ እና ሶሪያ የደረሰ ርዕደ መሬት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጠፈ
በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 9 ሆኖ የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ፥ በርካታ ህንጻዎችን በማፈራረሱ የነፍስ አድን ስራውን ፈታኝ አድርጎታል
ከባድ ነው የተባለው ርዕደ መሬት እስከ ሊባኖስ እና ቆጵሮስ ድረስ ንዝረቱ ተሰምቷል
ማዕከላዊ ቱርክ እና ሰሜን ምዕራባዊ ሶሪያ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ተከስቶባቸው በመቶዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በርዕደ መሬት መለኪያ (ሬክተር ስኬል) 7 ነጥብ 9 ሆኖ የተመዘገበው አደጋ በርካታ ህንጻዎችን በማፈራረሱም በፍርስራሽ ስር ያሉ ሰዎችን የማትረፍ ርብርቡ ቀጥሏል።
አደጋው በምሽት መድረሱም የነፍስ አድን ስራውን ፈታኝ እንዳደረገው ነው የተነገረው።
ኢርደም የተባለ የቱርኳ ጋዚያንቴፕ ከተማ ነዋሪ፥ “በ40 አመት ውስጥ እንደዚህ አይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም” ማለቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
“በጋዚያንቴፕ ከተማ አንድም ሰው በቤቱ ውስጥ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፤ ሁሉም ከቤቱ እየወጣ ሸሽቷል” ሲልም የአደጋውን አስከፊነት ገልጿል።የቱርክ የአደጋ መከላከል ተቋም በአደጋው እስካሁን የ76 ሰዎች ህይወት ማለፉን ነው ያስታወቀው።
ከ440 በላይ ሰዎችም መቁሰላቸውንና የሟቾቹ ቁጥር ማሻቀቡ እንደማይቀር ገልጿል።
በህንጻዎች ፍርስራሽ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለማትረፍ ግን ርብርቡ መቀጠሉን ነው የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ሱሌይማን ሶልዩ ለጋዜጠኞች የተናገሩት።
አንካራ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግላት የጠየቀች ሲሆን፥ በቀጣይ ሊከሰት ለሚችል አደጋም ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ አዛለች።
በሶሪያም በሃማ፣ አሌፖ እና ላታኪያ ግዛቶች ከ100 በላይ ሰዎች በርዕደ መሬቱ ምክንያት ህይወታቸውን ማጣታቸውን የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በ12 አመቱ የሶሪያ ጦርነት ተደጋጋሚ ጉዳት ያስተናገዱ ቤቶች በፍጥነት ወደፍርስራሽነት ተለውጠዋል ነው ያሉት የአይን እማኞች።
ንዝረቱ እስከ ሊባኖስ እና ቆጵሮስ ድረስ የተሰማው ርዕደ መሬት በአንካራም ሆነ በቤሩት ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ ተገልጿል።
ቱርክ ለመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ክፉኛ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
በፈረንጆቹ 1999 ኢዝሚት በተሰኘች ከተማ የደረሰ ርዕደ መሬት ከ17 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት መንጠቁ የሚታወስ ነው።
በ2011ም በምስራቃዊቷ ቫን ከተማ ከ500 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ርዕደ መሬት መከሰቱን ሬውተርስ በዘገባው አውስቷል።