ቱርክ በከባድ ርዕደ መሬት ተናጠች
የሀገሪቱን ዱዛሴ ግዛት ክፉኛ ያንቀጠቀጠው ርዕደ መሬት እስካሁን ከ40 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ እየተነገረ ነው
አደጋው ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉም ምክንያት ሆኗል
ቱርክ በከባድ ርዕደ መሬት መመታቷ ተነገረ።
ርዕደ መሬቱ የሀገሪቱ ሰሜን ምዕራባዊ ግዛት ከሆነችው ዱዝሴ ነው የተነሳው።
የቱርክ የአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን እንዳስታወቀው አደጋው በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 9 ሆኖ መመዝገቡን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው በርካታ ግዛቶችን እና ከተሞች ማዳረሱ የተነገረ ሲሆን፥ እስከ መዲናዋ አንካራ እና ኢስታንቡል ድረስ ንዝረቱ ተሰምቷል ተብሏል።
ከባዱ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በዱስዜ ግዛት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ምክንያት ሆኗል።
ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስም የኤሌክትሪክ ስርጭት በፍጥነት እንዲቋረጥ መደረጉን ነው አናዶሉ ያስነበበው።
አደጋው እስካሁን ያደረሰው ጉዳት ሪፓርት አልተደረገም ብለዋል የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ሱሌማን ሶይሉ።
ቢቢሲ ግን እስካሁን ከ47 በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል የሚል መረጃን አጋርቷል።
ከቱርኳ ትልቅ የንግድ ከተማ ኢስታንቡል በ230 ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኘው ዱዝሴ ከተማ በፈረንጆቹ 1999 የ845 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ከባድ ርዕደ መሬት ደርሶባታል።
በርዕደ መሬት መለኪያ 7 ነጥብ 2 ሆኖ የተመዘገበው አደጋ የከተማዋን ህንፃዎች ማፈራረሱን ተከትሎ ከ80 በመቶ በላይ የከተማዋ ህንፃዎች አደጋን እንዲቋቋሙ በአዲስ መልክ ተገንብተዋል።
ከ1999ኙ አስከፊ አደጋ ከወራት በኋላ ኢዝሚት በተሰኘችው ከተማ ከ17 ሺህ በላይ ሰዎችን የጨረሰ ርዕደ መሬት መከሰቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
ከሰሞኑ በተመሳሳይ በኢንዶኔዥያ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከ200 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ባቆሰለው አደጋ የተጎጂዎቹ ቁጥር አሁንም ድረስ እያሻቀበ ነው።