በቱርክ ርዕደ መሬት የሟች ቁጥር ከ21 ሽህ አለፈ
ፕሬዝዳንቱ የመልሶ የማቋቋም ስራ በሳምንታት ውስጥ እንጀምራለን ብለዋል
የቱርክ ፕሬዝዳንት በመሬት መንቀጥቀጡ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች መጎዳታቸው አስታውቀዋል
በቱርክ ርዕደ መሬት የሟች ቁጥር ከ21 ሽህ አለፈ
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲጺ ጣይብ ኤርዶጋን ለሀገራቸው ህዝብ ባደረጉት ንግግር “በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 21 ሽህ ደርሷል” ሲሉ አስታውቀዋል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት በመሬት መንቀጥቀጡ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች መጎዳታቸውንም አስታውቀዋል።
የቱርክ ፕሬዝደንት "የመሬት መንቀጥቀጡ ክብደት በጣም አስከፊ ነበር። ከዚህ በፊት ከነበረው ጋር ሊወዳደር አይችልም። እ.አ.አ. በ1999 ከነበረው የመጨረሻው የመሬት መንቀጥቀጥ በሦስት እጥፍ ይበልጣል" በማለት ሰኞ ዕለት ስለተከሰተው አውዳሚ አደጋ ተናግረዋል።
የቁሳቁስ ኪሳራን በተመለከተም በመቶ ሽህዎች የሚቆጠሩ ህንጻዎች ዶግ አመድ ሆነዋል ነው ያሉት።
"የመሬት መንቀጥቀጡ በ500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ውድመት አስከትሏል” ሲሉም አብራርተዋል።
ነገር ግን ጉዳቱን በተቻለ ፍጥነት ለመቋቋም ቃል የገቡት ፕሬዝዳንቱ "የተጎዱ ከተሞችን መልሶ የማቋቋም ስራ በሳምንታት ውስጥ እንጀምራለን" ብለዋል።
ኤርዶጋን ሀገራቸው የመልሶ ግንባታውን በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ እንደምታጠናቅቅም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት "አንዳንድ ወገኖች ከሁኔታው ለማትረፍ እየሞከሩ ነው" ሲሉ ያስጠነቀቁም ሲሆን፤ "በመሬት መንቀጥቀጡ ዞኖች ውስጥ ዘረፋና ሌሎች ወንጀሎችን የፈጸሙትን እንቀጣለን" ብለዋል።