ፊንላንድ፤ ቱርክ የኔቶ አባልነት ጥያቄዋን ካጸደቀች የጦር መሳሪያ ወደ ቱርክ ኤክስፖርት የማድርግ ሀሳብ አለኝ አለች
የፊንላንድ የመከላከያ ሚኒስትር “አንካራ የኔቶ አባልነት ማመልከቻችንን የምታጸድቅበትን ጊዜ መገመት አልቻልኩም” ብለዋል
ቱርክ፤ ፊንላንድ እና ስዊድን ለአንካራ የገቡትን ቃል ሲፈጽሙ የማጽደቅ ግዴታችንን እንወጣለን ብላለች
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) ለመቀላቀል ሂደት ላይ ያሉት ስዊድን እና ፊንላንድ በቅርቡ አባል እንደሚሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
ሁለቱ ሀገራት የኔቶ አባል እንዲሆኑ አሜሪካ እና ፈረንሳይን ጨምሮ 23 ሀገራት አጽድቀዋል። የቀሩት ሰባት ሀገራትም በቅርቡ እንደሚፈርሙ ቢጠበቅም ፤ቱርክ በሀገራቱ የኔቶ አባልነት ጥያቄ ስታነሳ እንደቆየች ይታወቃል፡፡
በዚህም የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ሁለቱ የኖርዲክ ሀገራት የገቡትን ቃል እስኪጠብቁ ድረስ ቱርክ የስዊድን እና የፊንላንድ የኔቶ አባልነት ጥያቄን ትቀበላለች ለማለት እንደማይደፍሩ በቅርቡ መናገራቸውም ያታወሳል፡፡
"ለሀገራችን የተገባው ቃል እስኪፈጸም ድረስ በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋማችንን እንጠብቃለን" ሲሉም ነበር ኤርዶጋን በአንካራ ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር የተደመጡት፡፡
ቱርክ ይህን ትበል እንጅ ፊንላንድ አንካራን ያግባባል ያለችውን አዲስ ካርታ ይዛ ብቅ ብላለች፡፡ ይህም ቱርክ የኔቶ አባልነት ጥያቄዋን በቶሎ ስታጸድቅ የተሻሉ ነገሮች እንደሚፈጠሩ ገልጻለች፡፡
የፊንላንድ የመከላከያ ሚኒስትር አንቲ ካይኮን እንደተናገሩት ቱርክ የኔቶ አባልነት ጥያቄያችን ስታጸድቅ ወደ ቱርክ የጦር መሳሪያ ኤክስፖርት ፈቃድ መስጠትን እንደሚያስቡ ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ “አንካራ የሀገራችንን የኔቶ አባልነት ማመልከቻ የምታጸድቅበትን የጊዜ ሰሌዳ መገመት አልቻልኩም” ብለዋል ካይኮነን ከቱርክ አቻቸው ሁሉሲ አካር ጋር በአንካራ ከተገናኙ በኋላ ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡
የቱርክ ገዥው ኤኬ ፓርቲ አንጋፋ ፖለቲከኛ እንደሚሉት ከሆነ ግን የአባልነት ጥያቄን የማጸደቁ ፍጥነቱ በፊንላንድ እና በስዊድን እጅ እንዳለና ይህም ሀገራቱ የቱርክ ጥያቄዎች በፍጥነት ሲያሟሉ የሚተገበር ይሆናል፡፡
የቱርክ ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኃላፊ እና የገዢው ኤኬ ፓርቲ አባል አኪፍ ካጋታይ ኪሊች በበኩላቸው ቱርክ የኖርዲክ ሀገራትን የኔቶ አባለነት ጥያቄን ለማጸደቅ "ምንም የሚስቸኩል ምክንያት እንዳልነበራት" ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
ኪሊክች"ሁሉም ነገር የፊንላንድ እና ስዊድን ነው... ከነሱ የምንጠብቀውን ነገር ሲያሟሉ የማጽደቅ ግዴታችንን እንወጣለን፣ ቃልም ጭምር ገብተንላቸዋል" ሲሉም አክለዋል።
እነሱ የገቡትን ቃል ሲተገብሩ መንግስታችን ለፓርላማ አቅርቦ የሚያጸድቅ ይሆንላም ነው ያሉት የቱርክ ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኃላፊ እና የገዢው ኤኬ ፓርቲ አባል አኪፍ ካጋታይ ኪሊች፡፡
በተያያዘ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ፤ ፊንላንድ ከቱርክ ድጋፍ ለማግኘት በአንካራ ላይ የተጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ማንሳት አለባት ሲሉ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
"ከፊንላንድ ወደ ቱርክ መሳሪያን ስለመላክን በተመለከተ ከፊንላንድ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር አንዳንድ ውይይቶች ተካሂደዋል፤ አንዳንድ ጀምር ንግግሮች አሉ፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተወሰኑ ነገሮችን ኤክስፖርት ማድረግ ይቻላል " ም ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡