በምዕራብ ቻይና ቲቤት በደረሰ ጠንካራ ርዕደ መሬት 100 ገደማ ሰዎች ህይወት አለፈ
ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 62 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች በፍርስራሾች ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል
ርዕደ መሬቱ ከምዕራባዊ ቻይና እስከ ኔፓል ድንበር ድረስ መሸፈኑን የቻይና የዜና ወኪሎች ዘግበዋል
በምዕራብ ቻይና ቲቤት በደረሰ ጠንካራ ርዕደ መሬት 100 ገደማ ሰዎች ህይወት አለፈ።
በምዕራብ ቻይና ቲቤት ማክሰኞ ዕለት በደረሰ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ 100 ገደማ ሰዎች መሞታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ወደ 1500 የሚጠጉ የእሳት አደጋ እና የነፍስ አድን ሰራተኞች በፍርስራሹ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለመፈለግ መሰማራታቸውን የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሺንዋ የዜና ወኪል የምዕራብ ቻይና ክልል የአደጋ መከላከል ዋና መስሪያ ቤትን ጠቅሶ እንደዘገበው 62 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የመሬት መንቀጥቀጡ በማግኒቲዩድ 7.1 እንደሚለካ እና ጥልቀቱም 10 ኪሎ ሜትር እንደሚደርስ ሲያሳውቅ ቻይና በበኩሏ በማግኒትዩድ 6.8 እንደሚለካ ይፋ አድርጋለች፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ የተጎጂዎችን ቁጥር ለመቀነስ እንዲሁም የተጎዱ ሰዎችን በአግባቡ ለማቋቋም ሁሉን አቀፍ የፍለጋ እና የነፍስ አድን ስራ መሰራት አለበት ብለዋል።
አደጋው ከደረሰበት ስፍራ በ20 ኪሜ ርቀት ላይ ሶስት የከተማ እና 27 የመንደር አሰፋፈሮች ሲኖሩ በአጠቃላይ ወደ 6,900 የሚጠጉ የህዝብ ብዛት ያላቸው ናቸው፡፡
በእነኚህ አካባቢዎች በአደጋው ከ1000 በላይ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ሺንዋ ዘግቧል።
ከአለማችን ረጅሙ ተራራ ከኤቨረስት ተራራ በስተሰሜን ምስራቅ 75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሂማሊያ ተራሮች ላይ የሚገኙ የዓለማችን ረጃጅም ከፍታዎችን ከፍታ ለመለወጥ የሚያስችል ጥንካሬ የነበረው ነው ተብሏል፡፡
በሥፍራው አከባቢ ያለው አማካኝ ከፍታ ወደ 4,200 ሜትር (13,800 ጫማ) ነው ሲል የቻይና የመሬት መንቀጥቀጥ ማዕከል በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡
ከኔፓል ዋና ከተማ ካትማንዱ 230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተከሰተው ርዕደ መሬት ነዋሪዎችን ከእንቅልፋቸው ቀስቅሶ ቤታቸውን ጥለው ወደ በጎዳና እንዲያሩ አድርጓቸዋል።
ከዚህ ባለፈ ለአደጋው ቅርበት ባላቸው በኔፓል ተራራማ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች ስለሚገኙበት ሁኔታ ግልጽ መረጃዎች አልወጡም፡፡
የቻይና፣ ኔፓል እና ሰሜናዊ ህንድ ደቡብ ምዕራብ ክፍሎች በስፍራው በሚገኙ የመሬት ውስጥ እቅስቃሴ ምክንያት በተደጋጋሚ በመሬት መንቀጥቀጥ ይመታሉ።
በነዚህ አካባቢዎች ከ1950 ጀምሮ 21 ርዕደ መሬቶች ሲከሰቱ በቅርብ ጊዜ የደረሰው እና አስከፊው በ2015 በኔፓል የተከሰተው ሲሆን፤ በዚህ አደጋ ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡