ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተበት የሚገኘው አዋሽ ፈንታሌ ነዋሪዎች ስለ አደጋው ምን ይላሉ?
ነዋሪዎች “ከዕሁድ ጀምሮ እየደረሰ የሚገኝው መንቀጥቀጥ ግን ቤቶችን የሚያፈራርስ እና በጣም አስደንጋጭ ነው” ብለዋል
መንግሥት የርዕደ መሬቱ ማዕከል በሆኑ በ12 ቀበሌዎች ላይ የጉዳቱን መጠን አሰሳ እያደረኩ ነው ብሏል
በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ሌሎች አካባቢዎች እየተፈጠረ የሚገኘው ርዕደ መሬት ከአከባቢውተሻግሮ በአዲስ አበባ እና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ንዝረቱ እየተሰማ ይገኛል፡፡
በተከታታይ በሬክተር ስኬል ከ4 ጀምሮ ዛሬ ሌሊት 5.8 ሬክተር ስኬል እስከተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው አስጊነቱ ከፍ እያለ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ሕዋ ሣይንስና አስትሮኖሚ ተቋም እንዲሁም የስነ ምድር ትምህርት ክፍል ባለሙያዎች በአፋር ክልል እየታየ የሚገኝው የመሬት ውስጥ እንቅስቃሴ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ አደጋን እንዳያስከትል ጥንቃቄ እንዲደረግ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡
በአፋር ክልል ገቢ ረሱል ዞን ዱለቻና አካባቢው ከሰሞኑ የተከሰቱ ተደጋጋሚ ፍንዳታዎች የእሳተ ገሞራ ምልክት ናቸው ተብሏል፡፡
በፍንዳታው የተስተዋለው ከፍተኛ ጭስ እና ቅሪትም ከታች ወደ ላይ እየገፋ የመጣ ቅልጥ አለት ስለመኖሩ ማሳያ ስለመሆኑም ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
በአዋሽ ፈንታሌ ቀበና ከሰም ስኳር ፋብሪካ አካባቢ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት ወይዘሮ ጸሀይ በአካባቢው የርዕደ መሬት ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ወራት መቆጠራቸውን ያነሳሉ፡፡
“መሬት መንቀጥቀጥ ከጀመረ አንድ ወር አልፎታል ነገር ግን መጠኑ ያን ያህል አስጊ ስላልነበረ ከዛሬ ነገ ይቆማል በሚል የአካባቢው ሰው ኑሮውን ቀጥሎ ነበር፤ ከባለፈው ዕሁድ ጀምሮ እየደረሰ የሚገኝው መንቀጥቀጥ ግን ቤቶችን የሚያፈራርስ እና በጣም አስደንጋጭ ነበረ” ብለዋል፡፡
ዱለቻ በተባለው አካባቢ በሴጌንቶ ቀበሌ ከፍተኛ ሙቀት እና ጭስ የሚተፋው እሳተ ጎመራ መሰል ፍንዳታ መከሰቱን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች በስፋት ወደ ሌሎች አካባቢዎች መዘዋወር መጀመራቸውን አል ዐይን አማረኛ ከነዋሪዎቹ ያገኝው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ሁኔታዎች ይሻሻላሉ በሚል ተስፋ እስከባለፈው ማክሰኞ ድረስ በአካባቢው እንደነበሩ የነገሩን ወይዘሮ ጸሀይ መሬቱ በከፍተኛ ደረጃ መሰነጣጠቅ መጀመሩ በአስፓልት ላይ ጉዳት ስላደረሰ መኪናዎች ላይገቡ ይችላሉ በሚል ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው አዋሽ 7 አካባቢ ዘመድ ጋር ተጠግተው እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡
ርዕደ መሬትቱ የሚፈጥረው ስሜት በጣም አስፈሪ እና አስደንጋጭ እንደሆነ የሚናገረው ብሩክ የተባለው ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ በአንድ ሰአት ውስጥ ከሁለት እና ሶስት በላይ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚፈጠርበት አጋጣሚ እንደነበር ገልጿል፡፡
“መንቀጥቀጡ ሲከሰት መኖሪያ ቤት እና ሰው በአየር ላይ እንደ ኳስ ሲነጥር ተመለከታለህ፤ ከዛ ባለፈም መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ክሊኒኮች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መፍረሳቸውን ተመልክቻለሁ፡፡
አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች መንቀጥቀጡ ሲደጋገም ውጪ ላይ የሚተኙ እስከ እኩለ ሌሊት ሲጠብቁ የሚያድሩ ሰዎችም ነበሩ” ሲል ስለ አጋጣሚው ተናግሯል፡፡
በተጨማሪም ሰገንቶ በሚባለው አካባቢ ሁለት አይነት ፍንዳታዎች ተከስተዋል፤ አንድኛው ፍል ውሀ እና ጭስ ብቻ የሚተፋ ሲሆን ሌላው ደግሞ ዲንጋይ እና ሌሎች እሳት መሰል ፍንጣቂዎችን ወደ ምድር የሚረጭ መሆኑን ነው ነዋሪው የሚናገረው፡፡
ማህበረሰቡ እየተመለከተ ባለው ነገር በመደናገጡ የቻለ ንብረቱን ይዞ ያልቻለ ደግሞ ቤተሰቡን ሰብስቦ ህይወቱን ለማትረፍ ወደ አዋሽ 70 እና አዋሽ 40 አካባቢዎች እየተፈናቀለ ይገኛል ብሏል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ የርዕደ መሬቱ ማዕከል ከሆኑ አካባቢዎች ነዋሪዎችን የማራቅ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
መግለጫው በአፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ማዕከላቸውን አድርገው የተለያየ መጠን ያላቸው የርዕደ መሬት ክስተቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠን እና በድግግሞሽ እያደጉ ይገኛሉ ብሏል።
መንግሥት በተለይ የርዕደ መሬቱ ማዕከል (epicenter) የሆኑት አካባቢዎችን በመለየት በ12 ቀበሌዎች ላይ መንግሥት ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን በቦታው በማሰማራት የጉዳቱን መጠን አሰሳ እያደረገ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡
በእነዚህ ቀበሌዎች ከሚኖሩ 80 ሺህ ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማራቅ ለማስፈር ርብርብ እየተደረገ ነው ብሏል መግለጫው፡፡
በተጨማሪም ርዕደቱ በማኅበራዊ አግልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ በኢኮኖሚ ተቋማት እና በመሠረተ ልማት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽዕኖ መንግስት በመከታተል ላይ ነው ተብሏል፡፡