በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የሚገኘውን የአፍሪካ ቀንድ ከኮሮና እና የአንበጣ ወረርሽኝ ጉዳቶች እንዴት መታደግ ይቻላል?
በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የሚገኘውን የአፍሪካ ቀንድ ከኮሮና እና የአንበጣ ወረርሽኝ ጉዳቶች እንዴት መታደግ ይቻላል?
በግጭት፣በረሃብ፣ በድርቅ፣በዴሞክራሲ እጥረት የሚታማው የአፍሪካ ቀንድ የበረሃ አንበጣ መንጋም ተጨማሪ ፈተናው ሆኗል፡፡ በተደጋጋሚ ከየመን የሚነሳው የአንበጣ መንጋ ኢትዮጵያ፣ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያና ሌሎች ሃገራትን ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጉን ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡ አሁን ላይ የበረሃ አንበጣና የኮሮና ቫይረስ በብዙ ችግሮች ውስጥ ተተብትቦ የቆየውን አካባቢ በድጋሚ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳይከቱት ያሰጋልም ይላሉ ባለሙያዎች፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኢኮኖሚስቱ ጌታቸው ተድላ (ዶ/ር) ከ አል-ዐይን ጋር ባደረጉት ቆይታ የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት የበረሃ አንበጣንና የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ቅድሚያ መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡ የዚህ መነሻቸውም የኮሮና ቫይረስ ቀደም ሲል ከነበረው የአንበጣ መንጋ ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ያስከትላል በሚል ነው፡፡ ምናልባትም ‹‹ አንደኛው የዓለም ጦርነትና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካደረሱት ችግር የበለጠ ጉዳት እንዳያመጡ ያሰጋል›› ሲሉም የግብርና ተመራማሪው ዶ/ር ጌታቸው ገልጸዋል፡፡
ጌታቸው ተድላ (ዶ/ር)
ሌላው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አዳነ ገላጋይም ከዶ/ር ጌታቸው ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ የምግብ ዋስትናውን ያላረጋገጠ አካባቢ በመሆኑ ኮሮናና የአንበጣ መንጋ በክልሉ (በምስራቅ አፍሪካ) ብዙ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ አዳነ ገለጻ በአንበጣ ጉዳት የደረሰውን ለማካካስ ከፍተኛ የመስኖ ልማት ሊከናወን ይገባል ብለዋል፡፡ወደ ልማት ያልገባ ውሃ ወደ ልማት ማስገባት አስፈላጊም ግደታም ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ ሁኔታዎችን የሚተንትኑና ትንብያ የሚሰጡ ባለሙያዎችን ማዘጋጀትና አስቀድሞ ለመከላከል ጥረት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አዳነ ቅድመ ጥንቃቄ የማይደረግ ከሆነ ከሌላው ጊዜ በከፋ መልኩ በአካባቢው ከፍተኛ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስቀድሞ ለመከላከል የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት እርስ በእርስ ተደጋግፈው መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ለህዝባቸው ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መስራት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹አሁን የምንገኝበት ጊዜ የሞት የሽረት ጊዜ ነው›› ያሉት ዶ/ር ጌታቸው ‹‹በኮሮና ወረርሽኝ መቀለድ በህይወት እንደመጫወት ነው የሚታየው›› ብለዋል፡፡ ከከተማ ውጭ ላሉ ዜጎችም ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገበ ጠቁመዋል፡፡ በአካባቢው ሃገራት የጸረ ተህዋሲያን መከላከያ ኬሚካል ርጭት ማካሄድ፣ በመገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ መረጃዎችን ማሰራጨት ይገባልም ብለዋል፡፡
ከየመን ቀይ ባህርን አቋርጦ የሚመጣው የአንበጣ መንጋም ሆነ የኮሮና ቫይረስ ድሃ አርሶ አደሮችን በከፋ ሁኔታ ችግር ላይ ሊጥል ስለሚችል መንግስታትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቀድመው አደጋውን መከላከል አለባቸው፡፡ አሁን ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ ከተሰራጨ ውሃና ሳሙና በአግባቡ የማግኘት ፈተና ያለባት አፍሪካ የበለጠ ልትጎዳ ትችላለች ብለዋል፡፡
ሁለቱም የግብርናና ምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች፣ ዶ/ር ጌታቸው ተድላና አዳነ ገላጋይ፣ መንግስታት በጋራ መስራት ከቻሉ፣ በተለይ ( የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት ) ኢጋድ፣ የጤና ባለሙያዎችን ምክር በሚገባ መተግበር፣ ቀደም ያሉ በቀጣናው ያሉ ችግሮች ያደረሱትን ጉዳት በመገንዘብ፣ በመተንተን እና አስቀድሞ በመጠንቀቅ በተለይም ደግሞ ከፍተኛ የግንዛቤ ስራ በመስራት የአፍሪካ ቀንድን ከችግሮች መታደግ ይቻላል ብለዋል፡፡