አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ በተሸከርካሪዎች ላይ ከ5 በመቶ እስከ 405 በመቶ ይደርሳል፡፡
አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ በተሸከርካሪዎች ላይ ከ5 በመቶ እስከ 405 በመቶ ይደርሳል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ስብሰባው የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል።
ቋሚ ኮሚቴው በስራ ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ለረጅም ጊዜ በስራ ላይ የቆየ በመሆኑ እና የማምረቻ ወጪን መሰረት አድርጎ የሚሰላ በመሆኑ ግልፅነት የሚጎድለው መሆኑን አንስቷል።
ይህን ለማስቀረትም አዲሱ አዋጅ በመሸጫ ዋጋ ላይ እንዲሰላ በማድረግ ለከፋይ እና አስከፋዩ ግልፅነት የሚፈጥር መሆኑን አመላክቷል።
በተጨማሪም ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በአካባቢ ደህንነት ላይ እያስከተሉት ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ከተወሰነ ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ለመገደብ እንዲሁም ለጤና ጎጂ በሆኑ ምርቶች ላይ ያለውን የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔን በመፈተሽ ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ መዘጋጀቱን ቋሚ ኮሚቴው አብራርቷል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ በተደረጉ ማሻሻያዎች ላይም ቋሚ ኮሚቴው ከ1,300 ሲሲ ያልበለጠ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ተሽካረካሪዎች እና ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ አዲስ በሃገር ውስጥ የሚገጣጠሙ፣ ሙሉ በሙሉ ተበትነው የቀረቡ፣ በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እንዲገጣጠሙ በከፊል ተበትነው የገቡ እና አዲስ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው በሚቀርቡት ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ30 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ እንደተደረገበት አንስቷል።
በተጨማሪም ከ1 ዓመት እስከ 2 ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ80 በመቶ ወደ 55 በመቶ እንዲሁም፥ ከ2 ዓመት እስከ 4 ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ130 በመቶ ወደ 105 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ ተደርጎበታል።
ከ4 እስከ 7 ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ230 በመቶ ወደ 205 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ መደረጉ ተጠቅሷል።
ከ7 ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ430 በመቶ ወደ 405 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ መደረጉም ነው የተነሳው።
ይህ ማሻሻያ መካከለኛ የገቢ ደረጃ ላይ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍልን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱንም ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።
በሲጋራ ላይ የተጣለው የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ በፓኬት በዋጋው 30 በመቶ እንዲሁም በፍሬ 5 ብር የነበረው በኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያው ተጨምሮ 8 ብር እንዲሆን መደረጉንም ነው የገለጸው።
በረቂቅ አዋጁ የታሸገ ውሃ ላይ ተጥሎ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ ከ15 በመቶ ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።
በቴሌኮም አገልግሎቶች ላይ እንዲጣል በኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጁ ቀርቦ የነበረው የ5 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲወጣ መደረጉም ነው የተገለፀው።
በተጨማሪም አዋጁ በማሻሻያው ከፀናበት ዕለት በፊት የባንክ ፍቃድ የተሰጣቸው እና አዋጁ ስራ ላይ ከዋለበት እለት አንስቶ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገር በሚገቡ እቃዎች ላይ ኤክሳይዝ ታክስ የሚጣለው እና የሚሰበሰበው፣ በኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/1995 በተሻሻለው ድንጋጌዎች መሰረት ይሆናል ተብሏል።
ይህም በአዲሱ ማስተናገድ በታክስ አስተዳደር ስርዓት ላይ ችግር ስለሚያስቀምጥ ገደብ መቀመጡ ተመላክቷል።
ከቅጣት ጋር ተያይዞ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ዝቅተኛውን የቅጣት ገደብ የማያስቀምጥ በመሆኑ አንቀጹ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሰው ከ3 ዓመት እስከ 5 ዓመት የእስር ቅጣት እና ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲጣል በሚል ማሻሻያ እንደተደረገበትም ተገልጿል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጁን በ4 ተቃውሞ፣ በ7 ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።
የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያው ዓላማ
በስራ ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ ኢኮኖሚው ከደረሰበት ደረጃ የተጣጣመ በማድረግ የኤክሳይዝ ታክስ የሚጣልባቸው ምርቶችን መከለስ፣ ከህብረተሰቡ ጤና አንጻር ከSpecific እና Ad Valorem አንዱ ወይም ሁለቱ የሚጣሉባቸው ዕቃዎችን መለየትና በተለየው አግባብ መሠረት እንዲጣል በማድረግ በምርቶቹ መጠቀም ሊከሰት የሚችለውን የጤና ችግር መቀነስ፣ የታክሱ መሠረት በማምረቻ ወጪ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሲፈጠሩ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቅረፍ በታክስ ከፋዩ ያለውን የተገማችነት ችግር ለመቅረፍ ብሎም ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ፣ በወጪ ንግድ ላይ እየተፈጠረ ያለውን በግብዓት ላይ የተከፈለውን የኤክሳይዝ ታክስ አመላለስ ችግር በመቅረፍ ለወጪ ንግድ አመቺ ሁኔታ መፍጠር፣ የኤክሳይዝ ታክስ ተደራራቢነትን ማስቀረት (ታክሱ የሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ በሚጣልበት ምርት ወይም አገልግሎት በመጨረሻ ምርቱ ላይ እንዲሆን ለማድረግ) መሆኑ ተገልጿል፡፡