መገጣጠሚያው በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (ዩኤኢ) እና በኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ትብብር የሚገነባ ነው
በኢትዮጵያ ሁለተኛው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ሊገነባ ነው
መገጣጠሚያው በዩኤኢ እና በኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ትብብር የሚገነባ ሲሆን መገጣጠሚያውን ለመገንባት የሚያስችለው ስምምነት አልፎዝ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በ700 ሚሊዬን ብር ያስገነባው ባለ 9 ወለል የገበያ አዳራሽ በተመረቀበት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተፈርሟል፡፡
ስምምነቱ በሃገር በቀሉ አልፎዝ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤት ሼህ አሊ ሁሴን እና በአል ኦታሚያን ዋና ስራ አስኪያጅ ሷሊህ ቢን ኦታይማን ሰዒድ ተፈርሟል፡፡
የ100 ሚሊዬን ዶላር ዋጋ እንዳለውም ነው በፊርማው ወቅት የተገለጸው፡፡
በገበያ አዳራሹ የምረቃ ስነስርዓት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ እና የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ከ1989 ዓ/ም ጀምሮ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ያደርግ ነበር የተባለለት አልፎዝ ኢንቨስትመንት በቡና እና በእንስሳት ግብይት እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ መሰማራቱ ተነግሯል፡፡
ባለፉት 20 ገደማ ዓመታት ከአንድ ቢሊዬን ዶላር የበለጠ የውጭ ምንዛሬ ለኢትዮጵያ ማስገኘቱንም ነው ባለቤቱ ሼህ አሊ ሁሴን የተናገሩት፡፡
ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ በሃገር ውስጥ የገጣጠማቸውን ሦስት አዳዲስ ሞዴል ተሽከርካሪዎች ባስተዋወቀበት ዕለት በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም እጀምራለሁ በሚል ማስታወቁ የሚታወስ ነው።