የኢትዮጵያ አየርመንገድ ወደ 19 ሀገራት የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ
19ኙ ሀገራት በአየርመንገዱ ላይ እግድ በመጣላቸው ምክንያት በረራውን ለማቋረጥ ተገዷል
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ወደ 19 ሀገራት የሚያደርገውን በረራ ለማቋረጥ ተገደደ
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ወደ 19 ሀገራት የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ
የኢትዮጵያ አየርመንገድ በ19 ሀገራት ወደሚገኙት 24 የበረራ መዳረሻዎቹ የሚያደርገውን በረራ ለማቋረጥ ተገደደ፡፡
አየርመንገዱ በረራዎችን ለማቋረጥ የተገደደው መዳረሻዎቹ የሚገኙባቸው ሀገራት ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ እግድ በመጣላቸው መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአየርመንገዱ ባልደረባ ለአል-አይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየርመንገድ በራሱ በረራዎችን አላቋረጠም፤ ሌሎች አየር መንገዶች እንደታገዱት ሁሉ የኢትዮጵያ አየርመንገድም መዳረሻዎቹ ያሉባቸው ሀገራት እግድ ስለጣሉ በረራውን አቋርጧል ብለዋል፡፡
ምንጫችን በመላውዓለም 127 መዳረሻዎች ያሉት አየርመንገዱ እንዳይበር እግድ የጣሉት መዳረሻዎች እነማን ናቸው የሚለውን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡
የተለያዩ ሀገራት የኮሮና የቫይረስ መኖሩ ሪፖርት ከተደረገባቸው ሀገራት የሚደረጉ በረራዎችን ቫይረሱ እንዳይስፋፋ በማሰብ ማገዳቸው የሚታውስ ነው፡፡
ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ
የኮሮና ቫይረስ መጋቢት 4፣ 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ እስካሁን 2 ኢትዮጵያዉያንና 4 የውጭ ዜጎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 4ቱ ማገገማቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በትናንትናው እለት አስታውቀዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት በማሰብ መንግስት ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ትምህርትቤቶች ለ15 ቀናት ዝግ ሆነው እንዲቆዩና ብዙ ህዝብ የሚሳተፍባቸው ስብሰባዎችም እንዲሰረዙ ወስኖ፣ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ከቫይረሱ ስርጭት ስጋት ጋር በተያያዘ ፍርድቤቶች ከመጋቢት 10-24 በከፊል ዝግ እንደሚሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት አስታውቋል፡፡
ከቻይና ውሀን ግዛት የተቀሰቀሰው ቫይረሱ እስካሁን 176 ሀገራትን ያዳረሰ ሲሆን ከ7,000 በላይ ለሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽን ብሎ የፈረጀው ኮሮና ቫይረሱ እስካሁን ከ200,000 በላይ ሰዎችን ማጥቃት ችሏል፡፡